ሀዋሳ፡ ታህሳስ 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጤና ጣቢያው አገልግሎት መደሰታቸውን በሀዲያ ዞን ፎንቆ ከተማ አስተዳደር የፎንቆ ጤና ጣቢያ ተገልጋዮች ተናገሩ፡፡
የጤና ጣቢያው አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ ግብዐት የማሟላት ስራን በትኩረት እየሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታዉቋል።
ከጤና ጣቢያው ተገልጋዮች መካከል አቶ አንሽሶ አኒሴ እና ወ/ሮ ፋጡማ ያሲን በሰጡት አስተያየት በጤና ጣቢያው ከዚህ ቀደም የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት እንደነበርና ሌሎች አገልግሎቶችንም በተገቢው እያገኘ እንዳልነበረ ጠቅሰዉ አሁን ላይ በጤና ጣቢያው እየተሰጠ ባለው አገልግሎት ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የማህበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድህን አባል በመሆን በአንድ ጊዜ በሚከፍሉት ተመጣጣኝ መዋጮ አመቱን ሙሉ የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ከጤና ጣቢያው ባለሙያዎች መካከል መላኩ ወልዴ፣ ደገፈ ካበቶና መሠረት ኃይሌ በበኩላቸው ቀንም ሆነ ማታ እየገቡ ለብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የፎንቆ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ቦጋለ እንዳሉት በጤና ጣቢያው ከካርድ ክፍል ጀምሮ እስከ ተመላላሽ የህክምና ድረስ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ የተቀላጠፈ እንዲሆን በየቀኑ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እንደሚገመገሙ ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ለጤና ጣቢያው ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመድኃኒት ግዥ መፈፀሙን ጠቁመው፣ በጤና ጣቢያው የሚሰጡ አገልግሎቶች ይበልጥ የተቀላጠፈ እንዲሆን የከተማ አስተዳደሩ አንዳንድ ያልተሟሉ የህክምና መሳሪያዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለማሟላት ጥረት ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል።
የፎንቆ ከተማ አስተዳደር ጤና ዩኒት መሪ አቶ ራህመቶ ያሲን እንደገለጹት በከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰቡን ጤና ለማጎልበት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ለማህበረሰብ ዐቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ትኩረት በመሰጠቱ በ2016 በጀት ዓመት 3ሺህ 910 አባወራና እማውራዎችን አባል በማድረግ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ የመድኃኒት ግዥ መፈፀሙ ገልጸዋል።
ይህንን መልካም ተሞክሮ በ2017 በጀት ዓመትም አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ራህማቶ በተለይ በጤና ጣቢያው የመድሃኒት እጥረት እንዳይኖር ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የፎንቆ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብርሃኑ አቡቴ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ በ2016 በጀት አመት ከፍሎ መታከም ለማይችሉ 899 ግለሰቦች የህክምና ወጪ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው በተያዘው በጀት ዓመትም ለ923 ከፍለው መታከም ለማይችሉ የከተማዉ ነዋሪዎች የህክምና ወጪ እንደሚሸፍንላቸው ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በጤና ጣቢያው ላይ እርካታ እንዲያገኝ እያደረጉ ካሉ ነገሮች አንዱ የጤና ባለሙያዎች ጥቅማ ጥቅም እንዲከበርላቸው በማድረጋችን ነው ሲሉም ተናግረዋል ።
ጤና ጣቢያው አሁን ከሚሰጠው አገልግሎት የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የአልትራ ሳውንድ ማሽንን ጨምሮ ሌሎች መሟላት ያለባቸውን የህክምና መሳሪያዎችን ከዞንና ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለማሟላት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ህዝቡ በግብርና ልማት ሥራዎች የሚያደርገው ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የኣሪ ዞን አስተዳደር ገለፀ
ምቹና ለኑሮ ተስማሚ አካባቢ ለመፍጠር የተፈጥሮ ሀብትን መንከባከብ ወሳኝ ነው – የኮሬ ዞን ግብርና መምሪያ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ ያለው የከተማ ልማት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን የፎንቆ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ተናገሩ