በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 6ኛ ዙር መርሐግብር 9 ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይካሄዳሉ

በ2024/25 የውድድር ዓመት በአዲስ አቀራረብ እየተካሄደ የሚገኘው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 6ኛ ዙር መርሐግብር 9 ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይካሄዳሉ።

በዚህም መሰረት ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ሁለት ጨዋታዎች ሲካሄዱ ዢሮና ከሊቨርፑል እንዲሁም የክሮኤሽያው ዳይናሞ ዛግሬቭ ከስኮትላንዱ ሴልቲክ ጋር ይጫወታሉ።

በስፔን ካታላን ግዛት በሚገኘው ሞንቲቪዲ ስታዲየም ዢሮና ከሊቨርፑል ጋር የሚያከናውኑት ጨዋታ ይጠበቃል።

በአሰልጣኝ አርኔ ስሎት የሚመራው የመርሲሳይዱ ክለብ በሻምፒዮንስ ሊጉ ያከናወናቸውን 5ቱንም ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለ ብቸኛው ክለብ ሆኖ ከተሳታፊ ክለቦች አናት ላይ ሆኖ የምሽቱን ጨዋታ ያከናውናል።

በሊቨርፑል በኩል ብራዚላዊው ግብ ጠባቂ አሊሰን ቤከር ከጉዳት በማገገም ከ11 ጨዋታዎች በኋላ የግቡ ዘብ ለመሆን ሰፊ ዕድል እንዳለው ተገልጿል።

ምሽት 5 ሰዓት ላይ 7 ጨዋታዎች የሚካሄዱ ሲሆን በጣሊያን ቤርጋሞ አታላንታ ከሪያል ማድሪድ የሚያከናውኑት ጨዋታ ይጠበቃል።

በአሰልጣኝ ጂያንፔሮ ጋስፓሪኒ የሚመራው አታላንታ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ሆኖ ሎስብላንኮዎቹን ያስተናግዳል።

የቤርጋሞው ክለብ በሴሪኣው 9 ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴሪአው መሪ ከመሆኑ በተጨማሪ በሻምፒዮንስ ሊጉ እስካሁን ሽንፈትን ካላስተናገዱ 3 ክለቦች መካከል አንዱ ሆኖ ይገኛል።

ክለቡ በሻምፒስ ሊጉ ካከናወናቸው 5 ጨዋታዎች መካከል 3 በማሸነፍ 2 በአቻ ውጤት ያጠናቀቀ ሲሆን በነዚህ ጨዋታዎች 11 ጎሎችን በተጋጣሚዎቹ መረብ ላይ ሲያሳርፍ የተቆጠረበት 1 ግብ ብቻ ነው።

የ15 ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በማንሳት ባለክብር መሆን የቻለው ሪያል ማድሪድ በበኩሉ በሻምፒዮንስ ሊጉ 2 ጨዋታዎችን ብቻ በማሸነፍ በደረጃ ሰንጠረዡ 24ኛ ላይ ይገኛል።

በሪያል ማድሪድ በኩል ሁለቱ ብራዚላዊያን ተጫዋቾች ቪኒ ጁኒዬር እና ሮድሪጎ ከጉዳት በማገገም በጨዋታው እንደሚሰለፉ ተነግሯል።

በተመሳሳይ ሰዓት ባየርሊቨርኩሰን ከኢንተርሚላን፣አርቢ ሌይፕዚች ከአስቶንቪላ፣ሬድቡል ሳልዝበርግ ከፒኤስጂ፣ሻክታር ዶኔስክ ከባየርንሙኒክ ፣ብረስት ከፒኤስቪ፣ እንዲሁም ክለብ ብሩጅ ከስፖርቲንግ ሊዝበን ይጫወታሉ፡፡

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ