ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ባለሙያዎች በኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ የኣሪ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል የቦርድ አባላት የሆስፒታሉን የ2017 ዓ.ም 2ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
ውይይቱን የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ኣታ፤ የኣሪ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ይሁን ጋሎ እና የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ምስጥሩ ሀሚዳኪ በጋራ የመሩ ሲሆን በጤናው ዘርፍ እየተስተዋለ ያለውን የመልካም አስተዳደርና የግብዓት እጥረት ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር እንደ ተቋም ክፍተቶች የነበሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተቋሙ ባለሙያዎች በተቋሙ በዋናነት የግብዓት እጥረት፣ ብልሹ አሰራር በተለይም መድሃኒት በህገ ወጥ መንገድ ለሌላ የግል ተቋሟት የሚያስተላልፉ የስነ ምግባር ችግር ያለባቸው ባለሙያዎች እንዳሉ አንስተዋል፡፡
አያይዘውም በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የትርፍ ሰዓት አገልግሎት ክፍያ፣ የበጀት አጠቃቀም ላይ ግልፀኝነት አለመኖር፣ የቡድንተኝነት እና መሰል ችግሮችን መንግስት እንዲፈታ ጠይቀዋል።
የጤና መድህን ገንዘብ በወቅቱ ሰብስቦ ለተቋሙ ገቢ ባለመደረጉ በታካሚዎች ዘንድ መጉላላት እየፈጠረ በመሆኑ መንግስት አስችኳይ ምላሽ እንዲሰጥ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክታዊት አሰፋ ጠይቀዋል፡፡
የባለሙያ ተነሳሽነት ለጤና አገልግሎቱ ውጤታማነት የላቀ ፋይዳ አለው ያሉት የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ሰራ አስኪያጅ ዶክተር ሚስጥሩ ሀምዳኪ፤ ጤናማ የእርስ በርስ ግንኙነት ላይ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ለተገልጋይ እና ለሙያው ክብር ሰጥተው ለሚሰሩ ባለሙያዎች ዕውቅና መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኣሪ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ይሁን ጋሎ በበኩላቸው የጤና ስራ በባህሪው በቡድንና በቅንጅት ካልተመራ ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ጠቁመው፤ በዞኑ ካሉ ሆስፒታሎች በአንዱና አንጋፋው የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ ያለው የአሰራር ችግር ባለሙያው ተረጋግቶና ከሙሉ ልቡ አገልግሎት እንዳይሰጥ እያደረገ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ይሁን አክለውም የመድሃኒት እጥረት፣ የተጀመሩ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች መቆም እና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን በወቅቱ ሲስተም ውስጥ አስገብቶ ከመምራት አንጻር የታዩ ጉድለቶችን በቀጣይ በማረም ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለመስጠት ይሰራል ብለዋል።
የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብረሃም አታ፤ ለዞኑና ዙሪያው ማህበረሰብ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ተቋም ሆኖ በአገልግሎት አሰጣጥ እየደከመ በመሆኑ ከሰራተኞች ጋር በችግሮቹ ዙሪያ በተደረገው ውይይት ግብዓት የሚሆን ሐሳብ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በቀጣይ የመልካም አስተዳደር ችግርን እያረሙ ማስቀጠል ይጠይቃል ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው፤ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ገንዘብ፤ የተጀመሩ የማስፋፊያ ግንባታዎች እና የባለሙያዎች ጥቅማ ጥቅም ጋር ተያይዞ በዞኑ እና በየደረጃው ካለው የመንግስት አካል ጋር በመናበብ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ማህበረሰቡ እንዲያገኝ ይደረጋል ብለዋል።
ዘጋቢ: ጳውሎስ አሚገሮ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ያለአንዳች ፀጥታ ችግር ተከብሮ እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ማዕከል ከአለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በክልሉ ከምባታ ዞን ዶዮገና ወረዳ የጀመረው የትሮፒካል የዶሮ ዝርያ ማሻሻያ ፕሮጀክት ውጤታማ እንዳደረጋቸው በፕሮጀክቱ የታቀፉ አርሶ አደሮች ተናገሩ
የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች የመሠረተ ልማት ስራዎችን ከህብረተሰቡ ጋር እየሠራ መሆኑን የኮሬ ዞን ኬሌ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ