የምናልመውንና የምናስበውን ብልፅግና እውን ለማድረግ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች የራሳቸው ሚና እንዳላቸው ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 25/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የምናልመውንና የምናስበውን ብልፅግና እውን ለማድረግ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች የራሳቸው ሚና እንዳላቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ።

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ግብረ ሰናይ ድርጅት በኮንሶ ዞን ካራት ዙሪያ ወረዳ በ18 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ማስጀመር የሚያስችለውን ስምምነት አድረጓል።

“ብሩህ ለነገ ልጆቻችን” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የካራት ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኩሴ ጭሎ ፕሮጀክቱ በወረዳው በ2 ቀበሌያት የሚተገበር መሆኑን ጠቁመው፥ በውሃ፣ ጤና፣ በትምህርትና ሌሎች ልማታዊ ስራዎች ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የኮንሶ ዞን ም/አስተዳዳሪና የውሃና ማዕድን ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ መሳይ አሰፋ  ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የዞኑን የልማት ክፍተት በመለየት፥ በውሃው ዘርፍ ለመሰማራቱ ስምምነት በማድረጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል ።

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በአገሪቱ በሚገኙ 11 ክልሎች፣ በ 51 ዞኖችና በ206 ወረዳዎች በልጆች ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ የድርጅቱ የፊልድ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ጥላሁን ናቸው ።

በአገሪቱ በሚገኙ አከባቢዎች በትምህርት፣ በጤና፣ በውሃ መሠረተ ልማት ፣ በልጆች አቅም ግንባታና ጥበቃ እንዲሁም በአካባቢ ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በኮንሶ ዞንም ለሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ ስኬታማነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማሞ  ሞሊሶ የምናልመውንና የምናስበውን ብልፅግና እውን ለማድረግ የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች የራሳቸው ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያም በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ አከባቢዎች ልማታዊ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ያወሱት አቶ ማሞ በኮንሶ ዞን ካራት ዙሪያ ወረዳም በንፁህ መጠጥ ውሀ ዙሪያ በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

የክልሉ መንግስት ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ማንኛውንም ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁሟል።

በመርሀ ግብሩ የሀይማኖት አባቶች፣ የአከባቢው ሽማግሌዎች፣ ህፃናትና እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት የታደሙ ሲሆን  በወቅቱ የፕሮጀክቱ አተገባበር ዙሪያም የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ከድርጅቱ ጋር  የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል ።

ዘጋቢ ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን