ሀዋሳ፡ ሕዳር 24/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዲላ ከተማ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማፋጠን በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
በመዋቅራዊ ፕላን ምክንያት ወደ ከተማው በሚካለሉ ቦታዎች ዙሪያ የፊዚካል እና ፋይናንሻል ጉዳዮች ጥናት ቡድን ሪፖርት ላይ የውይይት መድረክ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።
የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ የዲላ ከተማን ከሌሎች ከተሞች የዕድገት ደረጃ ጋር እኩል ለማራመድና በሀገር ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የከተማውን የቆዳ ስፋት በማሳደግ ከተሜነትን ለማስፋፋትና የህብረተሰቡን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ዝናቡ፥ ከዞኑ ዲላ ዙሪያ ወረዳ ወደ ዲላ ከተማ የተካለሉ አምስት ቀበሌዎችን ፊዚካልና ፋይናንሻል መረጃዎችን በአግባቡ በማጥናት የሁለቱንም መዋቅር ዜጎችን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ እኩል ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መልኩ ከተማውን ለማዘመን እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡
የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዳንኤል ሽፈራው በበኩላቸው በከተማው መዋቅራዊ ፕላን ምክንያት ከዲላ ዙሪያ ወረዳ ወደ 3 ሺህ 239 ሄክታር የሚጠጋ መሬት ወደ ዲላ ከተማ የሚካለል መሆኑን ገልጸው፤ የከተማው መስፋፋት የህብረተሰቡን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻልና ከተማውን ከሌሎች የፌደራልና ክልል ከተሞች እኩል ተወዳዳሪ ለማድረግ ሚናው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
መዋቅሮቹ ወደ ከተማ መካለላቸውን ተከትሎ 288 የሚሆኑ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ወደ ዲላ ከተማ ይካተታሉ ያሉት የዲላ ዙሪያ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታሪኩ ታደሰ፥ የከተማው ዕድገት የህዝባችንን የጋራ ተጠቃሚነት ለማሻሻል ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ቢሆንም የዲላ ዙሪያ ወረዳ የውስጥ የገቢ አቅም በዚህ ምክንያት እንዳይዳከም አስፈላጊው ድጋፍ ለወረዳው እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ: ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

                
                                        
                                        
                                        
                                        
More Stories
እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
በትምህርት ሴክተር የመረጃ አያያዝ ውጤታማነት ዙሪያ በኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በትምህርታቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋና ቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ