ኮሌጁ አሁንም ከመንግስት መደበኛ በጀት ውጪ በራሱ በጀት ሌሎች ትልልቅ ኘሮጀክቶችን ቀረፆ እየሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ኮሌጁ በፌደራል ስራና ክህሎት ሚኒስቴር ስር ከሚገኙት አምስት የግብርና ኮሌጆች መካከል አንዱ ሲሆን ከሀገሪቱ ከሁሉም ክልሎች የሚመደብለትን ተማሪዎች ተቀብሎ እያሰለጠነ ይገኛል፡፡
የኮሌጁን እና የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ይፈታሉ ተብሎ የታመነባቸው ኘሮጀክቶችን በመቅረጽ ከፌደራል ስራና ክህሎት ሚኒስቴር በጀት ተፈቅዶለት የሚያስገነባቸው ኘሮጀክቶች የዘመናዊ ተማሪዎች መመገቢያ ኩሽና፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ መሆናቸውን የገለፁት የኮሌጁ አስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ዲን አቶ ግርማ ለገሠ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ከሶስቱ ካፒታል ኘሮጀክቶች መካከልም ዘመናዊ የተማሪዎች መመገቢያ ኩሽና በ30 ሚሊየን 356 ሺህ 660 ብር እየተገነባ እንደሚገኝ አቶ ግርማ ተናግረው፤ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኤሌክትሪክ ሀይል በመጠቀም በአካባቢ ደን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት እንደሚያስቀርና አፈፃፀሙ አሁን ላይ 95 በመቶ መድረሱን አብራርተዋል፡፡
በ113 ሚሊየን 540 ሺህ ብር እየተገነባ የሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ደግሞ በአንድ ጊዜ ከ2 ሺህ በላይ ህዝብ መያዝ እንደሚችልና በሚዛን አማን ከተማ የሚታየውን የመሰብሰቢያ አዳራሽ እጥረት እንደሚቀርፍ ከዚያም ሲያልፍ ኮሌጁ አከራይቶ ገቢ ያገኛል ሲሉ አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ አፈፃፀሙም 65 በመቶ ላይ እንደሚገኝ በመጠቆም፡፡
ሌላኛው የአካባቢውንና የኮሌጁን ማህበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ይቀረፋል ተብሎ የታመነው የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ አፈፃፀሙ ወደ 99 በመቶ መድረሱንና በ300 ሜትር ጥልቀት ላይ የወጣውን ውሃ ከዋና ውሃ መስመር ጋር አገናኝቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ብቻ ይቀራል ብለዋል፡፡
ከሚኒስቴር መስሪያ ቤት በጀት ተይዞ ከሚገነቡት ከእነዚህ ኘሮጀክቶች ባለፈ፤ ኮሌጁ የራሱን ወጪ በራሱ ገቢ ለመሸፈን በማቀድ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች እንዳሉም አቶ ግርማ ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ሁለት ሺህ የእንቁላል ዶሮ እርባታ መጀመሩን እንዲሁም 8 ሺህ ተጨማሪ ለማድረግ ቤት እየተገነባ እንደሆነም ገልጸዋል።
የአካባቢውን ወተት ፍላጎት መሠረት በማድረግ 26 የወተት ላሞች እርባታ ለማከናወን ቦታ ተለይቶ ቤት እየተገነባ እንደሚገኝም አቶ ግርማ አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ወሰኑ ወዳጆ – ከሚዛን ጣቢያችን

More Stories
ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በብዝሃነት ውስጥ የሚንፀባረቁ የመረዳዳትና የአብሮነት በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና የየዞን ከፍተኛ አመራሮች በሣውላ ማረሚያ ተቋም አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ልየታ ተካሄደ