ሀዋሳ፡ ሕዳር 24/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ ያሉ የገቢ አማራጮችን በተገቢው አሟጦ ከመሰብሰብ አንፃር ያሉ ውስንነቶች ማረም እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ገልጿል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ከክልልና ዞን ምክር ቤት የህዝብ ተወካይ አመራሮች እና የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አመራሮች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ያሉ የገቢ አማራጮችን በተገቢው አሟጦ ከመሰብሰብ አንፃር ያሉ ውስንነቶች ማረም ይገባል።
በተለይ በክልሉ በገቢ አሰባሰብ ዘርፍ ጎልተው የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውን የተናገሩት አፈ ጉባኤው ከእነዚህም የህገ-ወጥ ደረሰኝ መበራከት፣ የገጠር መሬት መጠቀሚያ እና የእርሻ ስራ ገቢ ግብር በክልሉ አዋጅ መሠረት ሙሉ በሙሉ መተግበር አለመቻሉን ጠቁመዋል።
የግብር ከፋዮች የደረጃ ሽግግር ላይ የሚነሱ ችግሮች ተቀርፈው በህዝብ የሚቀርቡ የመልማት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በክልሉ ገቢ አሰባሰብ ላይ የገቢ አማራጮችን በሚገባ ተጠቅሞ በመሰብሰብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ አለብን ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ እንደገለፁት፤ በ2017 የክልሉን መንግስት ወጪ 58 ከመቶ በገቢ ለመሸፈን በክልል ምክር ቤት አፀድቆ በየደረጃው ካሉ የገቢዎች መዋቅር ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ ወደ ስራ ተገብቷል።
በክልሉ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት በአግባቡ ገቢ ሰብስቦ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲቻል በክልሉ የሚገኙ ምክር ቤቶች በተገቢው ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ ከ59ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች 5ሺህ ብቻ የደረጃ “ሀ” እና ደረጃ “ለ” ግብር ከፍዮች መሆናቸው ወ/ሮ ህይወት ጠቁመዋል።
በክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊና የደንበኞች አገልግሎት ገቢ አወሳሰንና አሰባሰብ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ወንዱ ታደሰ፤ በመድረኩ ላይ የክልሉ የገቢ አሰባሰብ ስራ በሚመለከት በዝርዝር ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በዚህም በክልሉ ባለፉት 4 ወራት 3.2ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ መቻሉንና 80 ከመቶ መፈጸም መቻሉን ጠቁመዋል።
የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት ሀሳብና አስተያየት የገቢ ዘርፍ ለሁሉም ስራዎች ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ በየአካባቢው የሚነሱ የልማት ችግሮችን ለመፍታት ገቢ ላይ ጠንካራ ስራ መስራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በክልሉ ሰፊ የገቢ አማራጮች ያሉ ሲሆን እነዚህን በተገቢው አሟጦ ለመጠቀም በየደረጃው የሚገኙ አካላት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የክልልና የዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች የክልልና የዞን አመራሮችና የህዝብ ተወካዮች ተሳታፊዎች ሆነዋል።
ዘጋቢ: ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ችግሮችን ለመቋቋም መሠል ልማታዊ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ
በኮሌጁ እየተከናወኑ የሚገኙት ነባር ካፒታል ኘሮጀክቶች እየተገባደዱ እንደሚገኙ የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ገለፀ
የምናልመውንና የምናስበውን ብልፅግና እውን ለማድረግ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች የራሳቸው ሚና እንዳላቸው ተጠቆመ