የኣሪ ብሔረሰብ “ድሽታ ግና” ዘመን መለወጫ ክብረ በዓል በድምቀት እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ታህሳስ 01/2017 ዓ.ም የሚከበረው የኣሪ ብሔረሰብ “ድሽታ ግና” ዘመን መለወጫ ክብረ በዓል በድምቀት እንዲከበር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የኣሪ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን እና የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ በጋራ አስታውቀዋል።
በየዓመቱ በብሔረሰቡ ዘንድ ልዩ ትኩረትና ቦታ ተሰጥቶት ዘመን መለወጫ ክብረ በዓሉ እንደሚከበር የኣሪ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሀላፊ አቶ አብርሃም በዳና ገልፀዋል።
መረዳዳት፣ አብሮነት፣ ሠላም፣ ጽዳትና ውበትና ሌሎች እሴቶች ያሉት “ድሽታ ግና” ዘመን መለወጫ ክብረ በዓል በየዓመቱ በወርሃ ታህሳስ 1 እሴቶቹን በጠበቀ መልክ በጎሳ መሪዎች (ባቢዎች)፣ በሀገር ሽማግሌዎች እና ከመላው ኣሪ ብሔረሰብ በተጨማሪ በመላው ኢትዮጵያውያን በድምቀት እንደሚከበርም አቶ አብርሃም አብራርተዋል።
በዓሉ ህዝባዊ በዓል ሆኖ መከበር ከጀመረ ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ እንደሚከበር የገለፁት አቶ አብርሃም፤ በዓሉ ከቤተሰብ ደረጃ ጀምሮ ወረዳ ድረስ አልፎ በአዲስ አበባ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከብሮ ከፊታችን ታህሳስ 01/2017 ዓ.ም በጂንካ ሁለገብ ስታዲየም በዓሉ ይጠቃለላል ብለዋል።
በዓሉ አካባቢው እንዲነቃ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኣሪ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሀላፊ ከቶ ኤልያስ ቃሾ ናቸው።
ለበዓሉ ድምቀት ከዚህ ቀድም ከነበረው ለየት ያለ ዝግጅት መደረጉን አቶ ኤልያስ ገልፀው፤ አካባቢውን ለዓለም የሚያስተዋውቁ አስጎበኚ ማህበራት፣ አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።
ከበዓሉ እሴቶች መካከል አንዱ ጽዳትና ውበት ሲሆን ይህንንም ከኮሪደር ልማት ጋር በማስተሳሰር በልዩ ትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
አጠቃላይ የበዓሉ ቅድመ ዝግጅት በኮሚቴ እየተመራና እየተገመገመ የሚገኝ ሲሆን ቅድመ ዝግጅቱ መጠናቀቁን የገለፁት ሀላፊዎቹ ሕዳር 28/2017 ዓ.ም ከፋን ኢትዮጵያ ጋር በመቀናጀት ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት ታላቁ ሩጫ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ታህሳስ 1/2017 ዓ.ም ከፌደራል፣ ከክልል ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ ከአጎራባች ዞኖችና መዋቅሮች ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስትና ሌሎች ዕንግዶች በተገኙበት በዓሉ በጂንካ ሁለገብ ስታዲየም በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት እንደሚከበር አስታውቀዋል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/