በባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ዘርፍ የሚገኙ አቅሞችን በመጠቀም ለኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ድርሻ ሊኖረው እንደሚገባ ተገለጸ

በባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ዘርፍ የሚገኙ አቅሞችን በመጠቀም ለኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ድርሻ ሊኖረው እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ዘርፍ የሚገኙ አቅሞችን በመጠቀም ለኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክት ለማስቻል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡

ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት የሴክተሩን ጉባዔ ከክልሉ ብዝሃ ዋና ከተማ አንዷ በሆነችው ታርጫ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ፥  ቢሮው የህዝባችን አንድነትና ትስስር ለማጠናከር ልዩ ተልዕኮ የተጣለበት በመሆኑ ለተግባሩ መሳካት በተቀናጀ ጥረት እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በባህል፣ በኪነ ጥበብ፣ በስነ ሥዕል፣ በቱሪዝም፣ በታሪክ፣ በቋንቋና በስፖርት ዘርፍ የሚገኙ አቅሞችን አሟጥጦ በመጠቀም ለኢኮኖሚ ዕድገት ጉልህ ድርሻ እንዲያበረክቱ በትኩረት እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል።

የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶችና እሴቶችን ለሕዝባችን ትስስርና ለህብረ ብሔራዊነት ግንባታ ቁልፍ መሣሪያ እንዲሆኑ ለማስቻል ተገቢ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፥ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፈጠር የማይክሮ ኢኮኖሚ ስብራትን ለመጠገን ሰፊ አቅም ያለው ተቋም መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ሴክተሩ 2017 1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ዋና ዋና አላማዎች ላይ ተመሥርቶ በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ ማስቀመጥ፤ የ2017 ዓ.ም ቀሪ ወራት የዕቅዱ ስትራቴጂ ግቦች ዋና  ዋና ተግባራት የአፈጻጸምና አመላካቾች ላይ የጋራ ግብ ስምምነት፣ ተቋማዊ የአሠራር ስርዓት በማሳለጥ ጠንካራ ተቋም መግንባት፣ ተቋማዊ የክትትልና ግምገማ ግብር መልስ በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ መስጠት እንዲሁም ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም የሚያቀራርብ አቅጣጫ በማስቀመጥ የጉባኤ ዋና አላማ መሆኑን ያሳወቁት የቢሮ ዋና ኃላፊ  ይህንን ታላቅ ተልዕኮ ጉባዔተኛው ወስዶ ተግባራዊ እንደሚያደርግም አሳስበዋል።

በውይይት መድረኩ የስድስቱም ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊዎች ሙያተኞች  የተሳተፉት ሲሆን ጉባኤው  ለሁለት ቀን እንደሚመከር ከመርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

ዘጋቢ፡ አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ቅርንጫፍ