በደረጀ ጥላሁን
የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ መሐመድ ሼይቾ ናቸው፡፡ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የስልጤ ዞን የአካል ጉዳተኞች ማህበርን በሰብሳቢነት ያገለገሉ ሲሆን ከ2015 ሰኔ ወር ጀምሮ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን ፕሬዘዳንት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በቅጽል ስማቸው “ማሜ ሞባይልና ሶላር” በሚል የሚታወቁት መሐመድ ሼይቾ በህይወት ተሞክሯቸው፣ እንዲሁም ባላቸው ሀላፊነት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!
ንጋት፦ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ መሐመድ፦ እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፦ በትውውቅ እንጀምር?
አቶ መሐመድ፦ ትውልዴ በስልጤ ዞን ላንፉሮ ወረዳ ጦራ ከተማ ነው፡፡ በተከሰተብኝ የአካል ጉዳት እስከ 12 አመቴ በእንፉቅቅ ነበር የምንቀሳቀሰው፡፡ ወላጆቼ ወደ አዲስ አበባ ወስደው ህክምና እንዳገኝ አድርገዋል። ከህክምናው በኋላ ቸሻየር ሰርቪስ ኢትዮጵያ ከተባለው ግብረ ሠናይ ድርጅት በተደረገለኝ የእግር ክራንችና የአካል ድጋፍ በመጠቀም መንቀሳቀስ ጀመርኩ፡፡
ቀጥሎ በአዲስ አበባ ትምህርት የጀመርኩ ሲሆን ከትምህርቴ ጎን ለጎንም ሊስትሮ እየሰራሁ ህይወቴን መምራት ጀመርኩ፡፡ እስከ 10ኛ ክፍል ተምሬ ማትሪክ ወስጃለሁ፡፡ ከዚያም በግል እየተማርኩ በአካውንቲንግ የትምህርት ዘርፍ ዲፕሎማ፣ ከዚያም በተመሳሳይ ዘርፍ ድግሪ ይዣለሁ፡፡ አሁንም በእስላሚክ ፋይናንስ ትምህርት ዘርፍ እየተማርኩ ነው፡፡ ባለትዳር ስሆን አራት ወንድና አንድ ሴት ልጆች አሉኝ፡፡
ንጋት፦ አሁን በምን ሥራ ላይ ይገኛሉ?
አቶ መሐመድ፦ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በኤሌክትሮኒክስ ንግድ የተሰማራሁ ሲሆን በወረዳዎች ላይ ቅርንጫፎችን ከፍቼ ከወንድሞቼ ጋር ሥራውን እያስኬድኩ እገኛለሁ፡፡
በ2016 ዓ.ም ቢቋረጥም በፀሀይ ብርሀን የሚሰራ የሶላር ምርት ከማይክሮ ፋይናንስ ጋር በመተባበር በብድር ለአርሶ አደሩ አቀርብ ነበር፡፡ ለዘጠኝ አመት የሰራሁት ይህ ሥራ ግን በአንዳንድ የአሰራር ክፍተቶች እና በዋጋ ግሽበት ምክንያት ተቋርጧል፡፡
ከዚህ ሌላ “ማይንድ ሴት” የተባለ አክሲዮን ማህበር በማቋቋም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለመሳተፍ ፕሮጀክት ተቀርጾ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በትምህርት ዘርፍ “ለስኬትና ለልህቀት እንተጋለን” በሚል መሪ ቃል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመክፈት በቀንና በማታ ተማሪዎችን ተቀብለን እያስተማርን እንገኛለን። በ2017 ዓ.ም ከሚመለከተው አካል እውቅና በማግኘት ኮሌጅ የከፈትን ሲሆን የመንግስትን የቅበላ መስፈርት ያሟሉትን እንመዘግባለን። ይህም በሂደት ወደ ድግሪ መርሀ ግብር ከፍ የሚል ነው፡፡
“ማይንድ ሴት” አክሲዮን ማህበር 64 አባላት አሉት፡፡ ማህበሩን በቦርድ ሰብሳቢነት እየመራሁ ነው፡፡ ከትምህርት ዘርፍ በተጨማሪም በኢንቨስትመንት ዘርፍም ለመሰማራት እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡ ከዚህ በፊት ከብት ማድለብ ፕሮጀክት ጀምሬ ያላለቁ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ እሱን ለመቀጠል እየሰራን ነው፡፡
የግንባታ ሥራዎችም በወራቤ፣ ሚቶ እና ጦራ ከተሞች ላይ የተለያየ የአፈፃፀም ደረጃ ያላቸው ፎቆችን እየገነባን ነው፡፡ በግል ያስገነባሁት ፎቅ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን የኤሌክትሮኒክስ ቅርንጫፍ ተከፍቶ እየተሰራበት ይገኛል፡፡
ከዚህ ባሻገር የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሶላር አሶሴሽን ማህበር ምክትል ሰብሳቢ ሆኜ እየሰራሁ ሲሆን በመንግስት እውቅና ያለን 22 አቅራቢዎች በአማራጭ ኢነርጂ ዘርፍ እንሰራለን።
እንደ ማንኛውም ዜጋ መንግስት ማግኘት የሚገባውን ግብር እከፍላለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ግንባር ቀደም ግብር ከፋይ ሆኜ በዞን፣ በወረዳም ተሸልሜያለሁ፡፡ በቀድሞ ደቡብ ክልልም ተሸላሚ ነበርኩ፡፡ በዚህም ዋንጫ፣ ሜዳሊያና የምስክር ወረቀጥ ተሰጥቶኛል፡፡ በተቻለኝ መጠን እንደ ዜጋ የሚጠበቅብኝን ግብር እየከፈልኩ እንደ አንድ አካል ጉዳተኛ ዜጋ ደግሞ መጠየቅ ያለብኝን መብቴን እጠይቃለሁ።
ንጋት፦ በአካል ጉዳተኞች ማህበር ዙሪያ መስራት የጀመሩት መቼ ነበር?
አቶ መሐመድ፦ ወደ ክልል ከመሄዴ በፊት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በስልጤ ዞን የአካል ጉዳተኞች ማህበርን የማደራጀት ሥራ ሰርቻለሁ፡፡ የመብት ማህበር እንደመሆኑ የአካል ጉዳተኞች መብት እንዲከበር፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዲሆኑ አዋጁን የማስረዳትና ተግባራዊነቱን የመከታተል ስራ እንሰራ ነበር፡፡ ለዚህም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተባባሪ እንዲሆኑ ጥረት እያደረግን እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ ሰርተናል፡፡
ንጋት፦ የክልሉ የአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን መሪ ሆነው ያከናወኗቸው ተግባራት ምንድናቸው?
አቶ መሐመድ፦ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን ፕሬዘዳንት የሆንኩት ከ2015 ሰኔ ወር ጀምሮ ነው፡፡ በዚህም በክልሉ በሚገኙ ሰባት ዞኖችና ሶስት የልዩ ወረዳ መዋቅሮች የሚገኙ አካል ጉዳተኞች የኢኮኖሚና ማህበራዊ መብቶቻቸው እንዲከበር የማድረግ፣ እንዲሁም መንግስታዊ ተቋማት ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ በማድረግ አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ ህጎች፣ ፖሊሲዎችና ደንቦች እንዲሻሻሉና ተግባራዊነታቸው እንዲገመገም በተቻለ መጠን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡
እያንዳንዱ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ አካል ጉዳተኞች የተለያየ ችግር ያለባቸው ሲሆን እነዚህንም ከሚመለከታቸው የመንግስት አካልና ከህብረተሰቡ ጋር በመነጋገር እንዲፈታ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህም የመንግስት መዋቅርን ተንተርሰን መብታቸው እንዲከበርና ሌሎች መሰረታዊ የሆኑ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፍላጎታቸው እንዲሟሉላቸው እየሰራን እንገኛለን፡፡ ይህን ስናደርግ ለሚፈጠሩ ተግዳሮቶች አማራጭ መፍትሄ በማስቀመጥ መፍታት የሚቻለውን እየፈታን ላልተፈቱት ደግሞ ከምሁራን ሀሳብ እያሰባሰብን መፍትሄ ለማስገኘት እየሰራን ነው፡፡
ንጋት፦ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይ የነበራችሁ ተሳትፎ እስከምን ድረስ ነበር?
አቶ መሐመድ፦ እንደ ማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ እንደሚመለከተው ዜጋ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይ ሰፊ ሥራዎችን ሰርተናል፡፡ እንደ ሀገር በአካል ጉዳተኞች የተፈጠሩ ክፍተቶች አሉ፡፡ መንግስትና አካል ጉዳተኞች እንዳይግባቡ የሚያደርጉ ምክንያቶችን በመለየት የአካል ጉዳተኞችን ሀሳብ በመሰብሰብ አጀንዳ ማስያዝ ተችሏል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ቢፈቱ የአካል ጉዳተኛውን ችግር ይቀርፋሉ ብለን ያሰብናቸውን ሶስት አጀንዳዎች በመለየት በኮሚሽኑ የአጀንዳ ልየታ መርሀ ግብር ማጠቃለያ ላይ አቅርበናል። ይህንንም በፌደራል ደረጃ በሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ላይ እንደ ጉዳት አይነት የሚወክሉ አምስት አካል ጉዳተኞች ካላቸው የትምህርት ዝግጅት እና አቅም አንፃር መርጠን ክልሉን ወክለው እንዲሳተፉ አጀንዳዎቹን አያይዘን ልከናል፡፡
ንጋት፦ አጀንዳዎቹን ቢጠቅሱልን?
አቶ መሐመድ፦ አካል ጉዳተኞችን የተመለከቱ ከሶስቱ አጀንዳዎች አንደኛው አካል ጉዳተኞችን ከላይ አስከ ታች ሊመራ ወይም ሊያስተዳድር የሚችል አንድ ተቋም ያስፈልጋል። ተቋሙ በኮሚሽን ይሁን በሚንስቴር ብቻ አካል ጉዳተኞችን የሚመለከት ያስፈልጋል፡፡
ሁለተኛው አካል ጉዳተኞች ፖለቲካ ተሳትፎ የላቸውም ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሌሎች ምክር ቤቶች አካል ጉዳተኛውን የሚወክል ወንበር የላቸውም፡፡ ድምፃቸው በሌሎች ይነገራል እንጂ በራሳቸው አንደበት አይነገርም፡፡
የሀገራችን ህጎችና ፖሊሲዎች አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ አይደሉም፡፡ ተፈፃሚነታቸውም እምብዛም ነው፡፡ ማሳያው የህግ አስገዳጅነትን የሚጠቅሰው አንቀጽ 41/5 የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በተመለከተ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደ መልኩ መንግስት ያደርጋል ነው የሚለው፡፡ አቅሜ አልቻለም ብሎ በየደረጃው ያለ የመንግስት አካል እንዲያንሻፍፈው /ለትርጉም እንዲያጋልጠው/ የሚጋብዝ ህግ ነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያስችል አጀንዳ ቀርቧል፡፡
ሶስተኛው በአዋጅ ደረጃ የህንፃ አዋጅ አሳንሰር /ሊፍት/ መጠቀም የሚያስገድደው ከሶስተኛ ፎቅ በላይ ላለው ነው፡፡ ይህ ለአካል ጉዳተኛ ሳይሆን ለጉዳት አልባው ዜጋ ነው፡፡ ጉዳት የሌለበት እስከ ሶስተኛ ይደርሳል፡፡ ከዚያ በኋላ ስለሚደክመው ሊፍት ያስፈልገዋል እንደ ማለት ነው የኛ ግንዛቤ፡፡ ስለዚህ ለእንደዚህ አይነቱ ችግር ተዳርገናልና ተስተካክሎ አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ ያደረገ አዋጅ ይቀረጽ የሚል ነው፡፡
ንጋት፦ በክልሉ የሚገኙ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ምን ያህል ይሆናል?
አቶ መሐመድ፦ አካል ጉዳተኛ አባላት በቁጥር ደረጃ ስናየው መነሻው ጥቂት ሊሆን ይችላል፡፡ ግንዛቤው ባላቸው አካል ጉዳተኞች አማካይነት በመቀስቀስ በየአካባቢው የሚኖሩ ጉዳት ያለባቸው ጉዳቱ ከተረጋገጠ የማህበሩ አባል ይሆናሉ፡፡ መታወቂያ የለህም ተብሎ አገልግሎት አይነፈግም፡፡ ድጋፍም ይፃፍለታል።
በክልል ደረጃ 23 ሺህ አካባቢ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን መረጃው ያሳያል። ይሁን እንጂ መረጃው የተጣራ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም በሀገራችን ያሉ አካል ጉዳተኞች ቁጥር በውል የሚታወቅ አይመስለኝም፡፡
በየገጠሩ የአካል ጉዳት ያለባቸው ዜጎች መረጃ በትክክል ይመዘገባሉ ወይ? የሚለው የሁሉም ጥያቄ ነው፡፡ በዘር በሚተላለፉ በአንድ ቤት ሶስትና አራት አይነ ስውራን የሚፈጠሩበት፣ እንዲሁም የእንቅስቃሴ ችግር ያለባቸው ይኖራሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እንዲያሻቅብ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ የአካል ጉዳተኞችን ቁጥር በጥናት ተረጋግጦ እስካልቀረበ ድረስ በዚህ ልክ ብሎ መገደብ ያዳግታል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በልመናም ይሁን በተለያዩ በሥራ አጋጣሚዎች የመውጣት እድል የገጠማቸው ናቸው የመቆጠር እድል የሚያገኙት፡፡ ስለዚህ የአካል ጉዳተኞችን ቁጥር ገድቦ መናገር ምቾት አይሰጥም፡፡ ከዚህ አኳያ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ድረስ ያሉት አካላት በዚህ አካሄድ የሚጠቀሙ በመሆኑ ያልተጣራም ቢሆን ግምታዊ ቁጥር ነው የምናስቀምጠው፡፡
ንጋት፦ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ለአካል ጉዳተኞች የሚያደርገው ድጋፍ ምን ይመስላል?
አቶ መሐመድ፦ ህብረቱ በሁሉም የዞንና ልዩ ወረዳ መዋቅሮች እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የክልሉ መንግስት የምንፈልገውን ስንጠይቅ ምላሽ ይሰጠናል፡፡ በ2016 ዓ.ም በክልል ደረጃ የአካል ጉዳተኞች በዓል ስናከብር ሙሉ ካብኔው፣ እንዲሁም የዞን አመራሮችና በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚመለከታቸው አካላት ከፌደራል ጭምር ተጋብዘው ለየት ባለ መልኩ ተከብሯል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይም የክልሉ ርእሰ መስተዳድር እና አፈ ጉባኤ የተገኙ ሲሆን በአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው ተደርጓል፡፡
ከዚያ በኋላ ግንዛቤው ስለተፈጠረ እና የሚመለከታቸው አካላት ሀላፊነት ወስደው ስለሚሰሩ ለምንጠይቀው ጥያቄ ወቅታዊ ምላሽ እየተሰጠን ጥሩ ጅምር መኖሩን አስተውለናል፡፡ በሌላ በኩል የሚደረገው ድጋፍ ፍሬ እንዲያፈራ እና ለሌሎችም ምሳሌ እንዲሆን የተሰሩ ሥራዎች አፈፃፀም ተግምግሞ ውሳኔ የሚሰጥበት ሁኔታ ስለሚቀር መስራትን ይጠይቃል፡፡
ንጋት፦ አካል ጉዳተኞች ሰርተው እንዲለወጡ ምን ማድረግ አለባቸው?
አቶ መሐመድ፦ ሀገራችን ያለችበት የኢኮኖሚ ደረጃ ይታወቃል፡፡ ሀገራችን የተፈጥሮ ጸጋ ባለቤት ብትሆንም የምንጠቀምበት ሁኔታ ደግሞ ራሱን የቻለ ተግዳሮት አለው። ይህን ተግዳሮት አልፈው የሚጠቀሙ ዜጎች የመኖራቸውን ያህል መቋቋም ሳይችሉ ቀርተው የማይጠቀሙ ዜጎች ብዙ ናቸው፡፡ ከነዚህም አካል ጉዳተኞች ይጠቀሳሉ፡፡
ከዚህ አንፃር አካል ጉዳተኞች ከሀገር ሀብት ከመጠቀም አኳያ የሚታየውን ክፍተት በመሙላት ተጠቃሚ መሆን አለባቸው። መድረክ ተመቻቸም አልተመቻቸም ተጋፍጠው የሀገርን ሀብት ተጠቅመው ሀገር ከእነሱ የምትፈልገውን ለማበርከት ትልቅ ሥራ ይጠበቃል፡፡ ይህን ማድረግ የሚችሉ ውስን ናቸው፡፡ ይህን ማድረግ ባለመቻላቸው ለሌላ ተደራራቢ ጉዳት የሚዳረጉም አሉ፡፡ ነገር ግን ይህን አልፈው ፊት የሚወጡ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ አስባለሁ፡፡
ንጋት፦ ከአካል ጉዳተኞች ምን ይጠበቃል ይላሉ?
አቶ መሐመድ፦ ጉዳት አለብኝ ብለን ካሰብን ያንን ጉዳታችንን አልፈን ከሀገር ተጠቃሚነት አንፃር ጉልህ ድርሻ መወጣት አለብን፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው እንደ ዜጋ የሀገር ሀብት ከኛ አቅም ጋር አገናዝበን መጠቀም ስንችልና ማመላከት ስንችል ነው፡፡ እኛ መጠቀሚያ መንገዱን ካለማመላከታችን የተነሳ አጋዥ አካል እናጣለን፡፡ ስለዚህ ከሀገር ሀብት እኩል ተጠቃሚ ለመሆን መንገዱን መጥረግና ፊት ለፊት መውጣት አለባቸው፡፡
አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ ሞጋችና ጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ሲሆን ለሌሎችም አርአያ መሆን ይችላሉ። እኔ አካል ጉዳተኛ ነኝ ብለው ጉዳታቸውን አምነው ተቀብለው ማስተናገድ አለባቸው፡፡ አካል ጉዳተኛ ነኝ በሚል ሰበብ ብቻ ወደ ኋላ መቅረት አያስፈልግም፡፡
ስለዚህ አካል ጉዳተኞች ጉዳታችሁን ታሳቢ አድርጋችሁ ማድረግ የምትችሉትን ለሚመለከተው አካል ለማሳወቅ ጥረት እንድታደርጉ እላለሁ፡፡ ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ሳይሆን አማራጭ ተስፋ በማሳየት አርአያ እንድትሆኑ የሚል መልእክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡
ምክንያቴ ደግሞ ከራሴ ተሞክሮ አኳያ ነው፡፡ አካል ጉዳተኝነቴ እግሬ ላይ ነው። የሚገባኝን እያደረኩ የተወሰነ ራሴንና በእኔ ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ለመደገፍ ሞክሬያለሁ፡፡ ከእኔ በላይ ተምሳሌት መሆን የሚችሉ ጀግና አካል ጉዳተኞች በአካባቢያችን፣ በሀገርና በአለም አቀፍ ደረጃ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡
ንጋት፦ ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለ?
አቶ መሐመድ፦ በአንድ ጀምበር የሚመጣ ለውጥ ባይኖርም የሚዲያ ሰዎች ትልቅ ሀላፊነት አለባቸው፡፡ የህሊና ግዴታም ነው፡፡ አካል ጉዳተኞች በየቦታው ሲገለሉ ይስተዋላል፡፡ ቤት ተዘግቶባቸው ቢያንስ የተፈጥሮ ብርሀን እንኳን ለማየት ያልታደሉ አሉ፡፡ በተለይ በየገጠሩ ያሉትን አስሶ የማውጣት ትልቁ ድርሻ የሚዲያው ነው፡፡ ሚዲያ የሚሰራውን ማንም አይሰራውም፡፡ ስለዚህ ሚዲያው በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ህብረተሰቡን በማንቃትና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን ከሰራ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡
ከዚህ ሌላ ከህግና ከፖሊሲ ጋር ተያይዞ ያሉ ክፍተቶች በሚዲያ አካላት የሚወጡና ማብራሪያ የሚሰጥባቸው መሆን አለባቸው። ዜጎች የሚዲያ አገልግሎት በእኩል የማግኘት መብት ስላላቸው ሀሳብ ያላቸው ወጥተው ሀሳባቸውን ማጋራት አለባቸው የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡
ንጋት፡– ለጋዜጣችን እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ ስለሆኑ በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ መሐመድ፡– እኔም እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
“ጉንፋን በአንቲባዮቲክስ መድሀኒቶች አይታከምም” – ዶክተር ሚስጥር አወቀ
እርቅ
የአምራች ዘርፉን የመቀላቀል ውጥን