የኣሪ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ድሽታ ግና በዓል በተለያዩ መርሃ-ግብሮች እየተከበረ ይገኛል

የኣሪ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ድሽታ ግና በዓል በተለያዩ መርሃ-ግብሮች እየተከበረ ይገኛል

በመጭው ወርሃ ታህሳስ 01/2017 ዓ.ም በኣሪ ዞን ማዕከል ጂንካ ከተማ በድምቀት የሚከበረው ድሽታ ግና በዓል መርሃ-ግብሮች አንዱ የሆነው የኣሪ ብሔረሰብ አለባበስና ባህላዊ ዕሴት ላይ ያተኮረ የቁንጅና ውድድር /Miss dishta gina/ በጂንካ ከተማ ተካሂዷል።

የጂንካ ከተማ ከንቲባ አቶ ስሳይ ጋልሺ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ ድሽታ ግና የመተሣሰብ፣ የመከባበር፣ የእርቀ ሠላም፣ የመረዳዳት፣ የጽዳትና ውበት ዕሴቶች ድምር በመሆኑ የዘንድሮውን በዓል ስናከብር በግለሰብና በቡድን ዕሴቶቹን በመተግበር ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በበጀት አመቱ በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረውን የከተሞች ኮሪደር ልማት በጂንካ ከተማም እየተተገበረ ባለበት ማግስት የሚከበር በዓል በመሆኑ ለከተማው ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል ነው ያሉት፡፡

የከተማውና የዞኑ ህዝብ የዘንድሮውን ድሽታ ግና በዓል ሲያከብር የኮሪደር ልማቱን በማስቀጠል ጂንካን ውብ፣ ማራኪና ለኑሮ ይበልጥ ተስማሚ ከተማ ለማድረግ እንዲሰሩ ከንቲባው ጠይቀዋል።

የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ በበኩላቸው፤ ድሽታ ግና ከባህላዊ ዕሴትነቱ ባሻገር የቱሪስት መስህብና እና የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግ ለተጀመረው ሥራ የፋሽን ውድድሮች የጎላ ሚና አላቸው ብለዋል።

የዘንድሮውን በዓል ለማድመቅ በተዘጋጀው የአልባሳት እና ዲዛይን ውድድር ለተሣተፉ አካላትና መድረኩን ላዘጋጁት ምስጋና ያቀረቡት አስተዳዳሪው የድሽታ ግና ዕሴቶች በበዓል ወቅት ማድመቂያነት ባለፈ የዕለት ተዕለት ተግባራችን ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በውድድሩ 1ኛ ደረጃ የወጣችው የቢኒ ባህላዊና ዘመናዊ አልባሳት ስፌት ተወዳዳሪዋ ወጣት በላይነሽ በዛብህ የ20 ሺህ ብር እና የዋንጫ ተሸላሚ ስትሆን 2ኛ የወጣችው ወ/ሪት ሥራውድንቅ መለሠ የ15 ሺህ ብር እንዲሁም 3ኛ ኤደን አራጋው የ10 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ለመርሃ-ግብሩ ስኬት የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አካላት፣ ለውድድሩ ተሣታፊዎች እንዲሁም ለዲዛይን ባለሙያዎች የዕውቅና ሠርተፍኬት እና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ጣቢያችን