ህዝቡን የሚለውጡ ልማቶችን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል የደቡብ ኦሞ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአምስት ዓመታት የተገኙ ድሎችን በማጽናት መላው ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ህዝቡን የሚለውጡ ልማቶችን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል የደቡብ ኦሞ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አስታውቋል።
“የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሐሳብ የፓርቲው 5ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል ዞናዊ ማጠቃለያ መድረክ በዲመካ ከተማ ተካሂዷል።
የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች በተለያዩ ዝግጅቶች የፓርቲውን 5ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን አክብረዋል።
መድረኩን የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በፀሎት የከፈቱት ሲሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን ሠላምና አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲረጋገጥ ጠይቀዋል።
በተለይ ከሁሉም ልማት ቅድሚያ የሚሰጠው የሠላም ጉዳይ ላይ ፓርቲውና መንግስት አበክረው እንዲሰሩ የጎሳ መሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮርና ቅቡልነት ያገኘ ፓርቲ መሆኑን የገለፁት የደቡብ ኦሞ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ታደሰ ጋልጶክ፤ ባለፉት አምስት አመታት በርካታ ስኬቶችን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ ማስመዝገቡን አመላክተዋል።
ፓርቲው በበርካታ ጎታች ችግሮች መካከል አልፎ የሚጨበጥ ለውጦችን ማስመዝገቡን ሀላፊው አብራርተዋል።
ጠንካራ ተቋማዊ ሪፎርምና ግንባታ፣ ዘላቂ ሰላም፣ ለዜጎች ጠንካራ ኢኮኖሚ፣ አምራች ኢንዱስትሪ፣ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻልና ምገባ መርሃ ግብሮች እና በሌሎችም የተከናወኑ ተግባራትን አቶ ታደሰ ለተሳታፊዎች አንስተዋል።
ሚዛናዊና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያፀና ሀገራዊ ፓርቲ በመመስረት ለኢትዮጵያ ብልጽግና ራዕይ መሰነቅ የጀመረበት አዲስ ምዕራፍ ላይ ይገኛል ሲሉ ኃላፊው ጠቅሰዋል።
በቀጣይ እጅ ለእጅ በመያያዝ የተጀማመሩ ሰፋፊ ልማቶችን ከዳር ለማድረስና የህዝቡ ብልጽግና ለማረጋገጥ በጋራ እንነሳ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የፓርቲው አምስት ዓመታት ጉዞ በሰነድ መልክ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
በትምህርት ሴክተር የመረጃ አያያዝ ውጤታማነት ዙሪያ በኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በትምህርታቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋና ቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ