ሀዋሳ፡ ሕዳር 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከጊዜ ወደ ጊዜ በሙዝ ምርት ተጠቃሚነታቸው እየጨመረ መምጣቱን በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡
በወረዳው ከ500 በላይ ሄክታር መሬት በሙዝ ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የወረዳው ግብርና፣ አከባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ጽ/ቤት ገልጿል፡፡
በአመያ ዙሪያ ወረዳ ስሬ ሸዋ ቀበሌ አርሶ አደር ነዋሪዎች መካከል ይስሃቅ አብርሃም፣ መንግስቴ ማዳ እና ሀዳዮ አታሳ በሰጡት አስተያየት፤ የተሻሻሉ የሙዝ ዝርያዎችን በማምረት ከቤት ውስጥ ፍጆታቸው ባለፈ ልጆቻቸውን እያስተማሩ፣ ማህበራዊ ኑሯቸውን ከመምራት አልፎ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውንም እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች በተለይ በፍራፍሬ በሳይንሳዊ ዘዴ በአነስተኛ መሬት አምርቶ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የመደገፍና የመከታተል ሥራ እየተሰራ መሆኑን የሰሬ ሸዋ ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘዉዴ ሾጋሞ ገልፀዋል።
አከባቢው የፍራፍሬ እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ ከዚህ ቀደም አጥጋቢ ባልሆነ ሁኔታ ሲመረት የነበረውን የሙዝ ምርት አሁን ላይ የተሻሻሉ የሙዝ ዝርያዎችን አርሶአደሩ በክላስተር አምርቶ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን በወረዳው የሆርቲካልቸር ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ በላይነህ አብራርተዋል።
በዞኑ አመያ ዙሪያ ወረዳ ግብርና፣ አከባቢ ጥበቃና ህብረት ሥራ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቢሻው ተስፋዬ በበኩላቸው፤ በወረዳው በሙዝ ምርት 515 ሄክታር መሬት ለመሸፈን መታቀዱን ገልፀው ከዚህም ውስጥ በመኸር ወቅት 398 ሄክታር መፈፀሙን ተናግረዋል።
በዚህ አከባቢ የሚመረተው የሙዝ ምርት ከጎረቤት ዞኖች አልፎ ለማዕከላዊ ገበያ ጭምር እየተላከ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ቢሻው አርሶ አደሮችም ሆነ ባለሙያዎች ለበለጠ ምርትና ምርታማነት ጭማሪ ሊጥሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ደረጀ ተፈራ – ከዋካ ጣቢያችን

More Stories
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በክልሉ ለሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ጀመረ
የቅድመ በሽታ መከላከል ተግባራትን በአግባቡ በመፈፀም ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ
የሸዋል ዒድ (ቀሊ ፍቼ) ባህላዊ ስርዓት በስልጤ