የኢኮኖሚ አቅም ውስንነት ያላቸውና አቅመ ደካሞችን ሁኔታ በማገናዘብ በዞኑ በዲላ ከተማ የመድኃኒት መደብር በመክፈት ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የጌዴኦ ዞን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ዳካ አስታውቀዋል።
የኢኮኖሚ አቅም ባገናዘበ መልኩ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ የመድኃኒት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ኃላፊው ገልፀዋል።
የኪሳቸውን አቅም በማይጎዳ መልኩ ተገቢውን አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን አንዳንድ በዞኑ የሚገኙ ተገልጋዮች ተናግረዋል።
በመድኃኒት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ጤና ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፥ ከዚህ ቀደም የነበረውን የመድኃኒት እጥረት እየተቀረፈ መምጣቱን ጠቁመዋል።
የመድኃኒት አቅርቦትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ የበጀት ውስንነት ችግር መኖሩን የጠቆሙት አቶ ወንድወሰን ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የዞኑ ቀይ መስቀል ቅ/ጽ/ቤት አባል በመሆን ማህበሩን በፋይናንስ ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በዲላ ማዕከል የቀይ መስቀል መድኃኒት መደብር ኃላፊ አቶ ምህረቱ በየነ እንዳሉት፤ ከህክምና ተቋማት በምርመራ በተረጋገጠው ማዘዣ መሠረት ኅብረተሰቡን የተፈለገውን መድኃኒት እንዲያገኝ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ለ24 ሰዓታት አገልግሎት እየተሰጠ ነው።
አገልግሎት ለማግኘት ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ተጠቃሚዎች ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ መሆኑን የጠቆሙት የፋርማሲ ቴክኒሻን ባለሙያ አቶ ዳዊት ክፍሌ ለዚህም በተለያዩ መንገዶች የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማጎልበት የተሠሩ ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አስረድተዋል።
በማዕከሉ የስኳር ህመም፣ የኮሌስትሮል፣ የደም ግፊትና የመሳሰሉት የመድኃኒት ዓይነቶች እንደሚገኙ የጠቆሙት ባለሙያው አገልግሎቱን ፈጣንና ቀልጣፋ በማድረግ ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ተገልጋዮችን በአገልግሎት አሰጣጥ ለማስደሰት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
አገልግሎቱን ሲያገኙ ካነጋገርቸው ተጠቃሚዎች መካከል አቶ ቴዎድሮስ ጫኔ እና ዮሴፍ መንገሻ በሰጡት አስተያየት፤ በዞኑ የዲላና ጨለለቅቱ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ ከተለያዩ ጤና ተቋማት የታዘዘላቸውን መድኃኒት ኪሳቸውን በማይጎዳ መልኩ ከማዕከሉ እያገኙ መሆናቸውን ጠቁመው ሁሉንም የተገልጋዮችን ያማከለ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
19ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
ለፕሮጀክቶች ስኬታማ ትግበራና ውጤታማነት የኢንዱስትሪ ተቋማትን ማዕከል ባደረጉ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ
ከጊዜ ወደ ጊዜ በሙዝ ምርት ተጠቃሚነታቸው እየጨመረ መምጣቱን በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ተናገሩ