ሀዋሳ፡ ሕዳር 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባለፉት ዓምስት ዓመታት በብልጽግና ፓርቲ መሪነት የዉስጥና የዉጪ ጫናዎችን በመቋቋም እንደ ሀገር ዉጤታማ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ።
“የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ እየተከበረ ነዉ።
በክብረ በዓሉ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንደገለጹት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በብልጽግና ፓርቲ መሪነት የዉስጥና የዉጪ ጫናዎችን በመቋቋም የብዝሃ ኢኮኖሚ መርህ በመከተል እንደ ሀገር ዉጤታማ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል።
በተለይም በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፉ ሀገር በቀል ስትራቴጂ በመከተል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የማስፈፀም አቅም በመፍጠር ክፍተኛ ለዉጥ ማስመዝገብ መቻሉንም ገልጸዋል።
ከእነዚህ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችም በበጋ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋትና በኮሪደር ልማት የታዩ ዉጤቶች ተጠቃሽ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በዲፕሎማሲ ዘርፍ የሀገር ዳር ድንበርን ከማስጠበቅ ጀምሮ የብሔራዊ ጥቅምን ከማስቀጠል አንጻር አበረታች ዉጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
ፓርቲው በክልሉ ለረጅም ጊዜያት ተጀምረው ባለመጠናቀቅ የህብረተሰቡ ከፍተኛ የቅሬታ ምንጭ የነበሩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በመመለሱ ረገድም የተሻለ ጥረት የተደረገበት ወቅት መሆኑን አንስተዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፓርቲው ትሩፋት መሆኑን ያነሱት ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ፥ ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህም በወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ የተሻለ ለዉጥ መመዝገቡን ገልጸዋል።
አሁን ላይ እንደ ሀገር እየታየ ያለዉን የኑሮ ዉድነት ችግር ለመቅረፍ የግብርና ስራዎች ላይ እየተሰጠ ባለዉ ትኩረት ለውጥ እየተመዘገበ ነዉ ብለዋል።
ክልሉ ገና ከተመሠረተ 3 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ከነባሩ ክልል የተላለፈውን ዕዳ ለመቀነስ የገቢ አቅምን በማሳደግ ወጪ ቆጣቢ የአመራር ስርዓት በመከተል 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዕዳ ተከፍሏል ብለዋል።
በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ከአጎራባች ዞኖችና ክልሎች ጋር እየተሰራ መሆኑን አንስተው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በተለይ ሁለንተናዊ ጤንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ከመፍጠር አንጻር የወባ በሽታና ሌሎችንም ለመከላከል ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በክልሉ ለተመዘገበው ዉጤት የአጠቃላይ ህዝቡ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ በሁሉም ዘርፎች ምላሽ የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት የህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።
“የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ የፓርቲው አጠቃላይ የአምስት ዓመታት እንቅስቃሴ በክልሉ ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ተሰማ እየቀረበ ነዉ።
በክብረ በዓሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የፓርቲው አባላት እየተሳተፉ ነዉ።
ዘጋቢ፡ አሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
ለፕሮጀክቶች ስኬታማ ትግበራና ውጤታማነት የኢንዱስትሪ ተቋማትን ማዕከል ባደረጉ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ
ከጊዜ ወደ ጊዜ በሙዝ ምርት ተጠቃሚነታቸው እየጨመረ መምጣቱን በኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ተናገሩ
ያሉንን ልዩነቶችን ተጠቅመው የህዝቦችን ነባርና ጠንካራ መስተጋብርን ለግጭትና ለሠላም እጦት የሚጠቀሙ አካላትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳወቅ ከሚዲያ አካላት እንደሚጠበቅ ተገለጸ