ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከማድረግም ባሻገር የነዋሪን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ተግባራትን ማከናወን ትኩረት የሚሰጥበት ጉዳይ  ነው –  የሙዱላ ከተማ አስተዳደር

ሀዋሳ፡ ሕዳር 16/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከማድረግም ባሻገር የነዋሪዉን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ተግባራትን ማከናወን ትኩረት የሚሰጥበት ጉዳይ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትየጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ገለፀ።

የተጀመሩ የልማት ተግባራትን በማስቀጠል የከተማው ህዝብ አንዳንድ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሔ ሊበጅላቸው እንደሚገባ የከተማዋ ነዋሪዎች ጠይቀዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ቢኒያም ታደሰ እንደተናገሩት፥ ከከተማዋ መስፋት ጋር ተያይዞ በርካታ የህዝብ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ያሉ እንደመሆኑ ከውስጥ ለውስጥ የመንገድ ስራዎች ጀምሮ ደረጃ በደረጃ የልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል።

የከተማ ጥያቄ የሚፈታው የውስጥ ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ ነው ያሉት ከንቲባው፥ የውኃና የውስጥ ለውስጥ መንገድ ብሎም የመብራት ተደራሽነት ትኩረት የሚሰጥባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀዋል።

ህብረተሰቡንና አጋር አካላትን በማሳተፍ ለከተማዋ ሁለንተናዊ ልማት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በቅርብ ጊዜ በከተማዋ የተሻለ ለውጥ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

ከንቲባው አክለውም ህብረተሰቡ በከተማዋ በሚሰሩ የልማት ተግባራት ከባለድርሻ አካላት ጎን በመሆን የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሙዱላ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ዘለቀ ገብርኤል በበኩላቸው፥ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በ2017 አዲስ ፕላን በማውረድ እንደሚሰራ ጠቁመው የህዝቡን የመሰረተ ልማት ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በከተማዋ ቤቶች ልማትም ከጊዜ ጊዜ ለውጦች እየታዩ እንደሆነ ገልፀው ለማናቸውም የኢንቨስትመንት ፍላጎት ሁኔታዎችን በማመቻቸት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

አንዳንድ የሙዱላ ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ በከተማዋ በርካታ የግል ኢንቨስትመንትና የልማት ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።

ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የመብራት መቆራረጥና የውኃ እጥረት ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ሊበጅላቸው እንደሚገባ ጠቁመው ለከተማዋ ብሎም ለአካባቢው ሁለንተናዊ ልማት ከባለድርሻ አካላት ጎን በመሆን የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን