ሀዋሳ፡ ሕዳር 15/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት የሚከበረው 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችን ሕዝቦች ቀን በዓል የክልሉን ብዝሃ ባህልና ፀጋዎችን ለማስተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር ነው ሲሉ የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ፤ ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ በሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል እና ታህሣስ አንድ የአሪ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ድሽታ ግና ቅድመ ዝግጅት ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢፌዲሪ ህገ መንግስት የፀደቀበትን ቀን አስመልክቶ በየአመቱ ህዳር 29 የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ተደርጎ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
ዘንድሮ በሀገር አቀፍ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው ህዳር 29 የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዘጋጅነት በአርባምንጭ ከተማ ይከበራል።
ለዚህም ከክልል ጀምሮ በተዋረድ ባሉ መዋቅሮች ልዩ ልዩ ዝግጅት እየተደረጉ ይገኛል።
የህገ መንግስቱ ትርፋት ከሆኑት አንዱ ራስን በራስ የማስተዳደር ሀገ መንግስታዊ መብት ነው ያሉት የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ፤ የዘንድሮ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በህዝቦች ጥያቄና የጋራ ፍላጎት በአዲስ መልክ ለተደራጀው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና አሪ ዞን ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል።
በአዲስ መልክ የተደራጀው አሪ ዞን እና ብዝሃ ማንነቶች ላለበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የራስን ባህል፣ ማንነትና ፀጋዎችን በሀገር አቀፍ ብሎም በአለም ለማስተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው በመግለጫቸው።
በበዓሉ ከሌሎች ክልሎችና ውጭ ሀገራት ለሚታደሙ እንግዶች የአሪን ብሔረሰብና አካባቢውን የሚያስተዋውቁ ስጦታዎች መዘጋጀታቸውን የገለፁት አቶ አብረሃም፤ በዓሉ እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር የጋራ ፀጋችን የሆነውን ህብረብሔራዊ አንድነታችንን የምናፀናበት ነው ብለዋል።
አቶ አብረሃም አያይዘውም ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ማግስት በየዓመቱ ታህሣስ 1 የሚከበረው የአሪ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ድሽታ ግና በዓል ዘንድሮ “ባህል ለሠላም፣ ለአንድነትና ለልማት” በምል መርህ በዞኑ መዲና ጂንካ ከተማ እንደሚከበር አስታውቀዋል።
ድሽታ ግና የእርቅ፣ የሠላም፣ የልማት፣ የመረዳዳትና የአንድነት ዕሴቶችን በመተግበር የሚከበር በዓል ነው ያሉት አቶ አብረሃም፤ የዘንድሮው ድሽታ ግና ከቤተሰብ ጀምሮ በዞን እና በአዲስ አበባ ዕሴቶቹን በጠበቀ መንገድ እንደምከበር አስታውቀዋል።
በመጨረሻም ለመላው የዞኑና የክልሉ ህዝብ ለ19ኛ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል እና የአሪ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ድሽታ ግና በዓል መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
አካል ጉዳተኞች መብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በቅንጅትና በጥምረት መስራት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ
አካባቢን በመጠበቅና በማጽዳት ምቹና ጽዱ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሁሉም የድርሻውን ልወጣ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ አሳሰቡ
ግለሰባዊ ነጠላ ትርክቶችን በጋራ በመታገል በመደመር እሳቤ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ