የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ

የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ

ልማት ማህበሩ በ10 አመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እና በዋና ዋና ግቦች ዙሪያ ከልዩ ወረዳው ወጣቶች ጋር የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል ፡፡

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪና የልማት ማህበሩ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞሳ ኢዶሳ በዚህ ወቅት እንደገለፁት ልማት ማህበሩ ከመንግስት ጎን በመሆን አባላቱንና አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር የብሔረሰቡን የባህል ማዕከል ግንባታን ጨምሮ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡

አሁን ላይ ልማት ማህበሩ የአመራር ሪፎረም በማድረግ ማህበረሰቡን የተሻለ ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እንዲሁም የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለማከናወን የ10 አመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባቱን ገልፀዋል፡፡

ለዚህም ልማት ማህበሩ በቀጣይ በረጅምና በአጭር ጊዜ አባላቱንና አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር ለማከናወን ያቀዳቸው የሆስፒታልና የአዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ እንዲሁም ሌሎችም ተግባራት ለማሳካት ወጣቱ የድርሻውን እንዲወጣ አቶ ሞሳ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

የልማት ማህበሩ ዋና የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ሙአዝ በድሩ በበኩላቸው አሁን የለውጡ መንግስት የፈጠረውን ምቹ እድል መጠቀም በልዩ ወረዳው ያሉ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በመለየት በቅንጅት የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

መድረኩ ላይ የልማት ማህበሩ የስራ ሃላፊዎችና የልዩ ወረዳው አመራሮች እንዲሁም ወጣቶች የተገኙ ሲሆን በቀጣይ በልማት ማህበሩ አስተባባሪነት ሊገነባ ለታቀደው ለወሸርቤ ለመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ የሚውል የ50ሺህ ካሬ ሜትር የመሬት ካርታ ርክክብ በማድረግ ተጠናቋል ።

ዘጋቢ፡ጅላሉ ፈድሉ