የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል።
ቢሮው የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሃላፊዎችና ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች በጀርሞች መላመድን መከላከል ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የጸረ ተህዋስያን መድኃኒቶች ያለ አግባብ ስራ ላይ በመዋላቸው መድኃኒቶቹ ከተህዋስያን ጋር በቀላሉ እንዲላመዱ እንደሚያስችላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ሀብቴ ገ/ሚካኤል፤ የፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል።
በዚህም በየዓመቱ በጸረ ተህዋስያን መድኃኒት መላመድ ምክንያት በዓለማችን ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለህልፈት እንደሚዳረጉ ሀላፊው አመላክተዋል፡፡
በፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ምክንያት ብዙ ዋጋ ተከፍሎባቸውና ዓመታትን ወስደው የተገኙ መድሃኒቶችን ዋጋ ቢስ የሚያደርግ ሲሆን ይህም በሽታውን ለማከም አስቸጋሪ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡
እንደ ሀገር በዘርፉ እየተስተዋለ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ለስኬታማነቱ ደግሞ የሁሉም ባለድርሻ አካላት እጅና ጓንት ሆኖ መሥራት ወሳኝ መሆኑን ነው አቶ ሀብቴ ያስገነዘቡት።
ከህዳር 9 እስከ 15 የጸረ ተህዋስያን መድኃኒት በጀርሞች መላመድን ለመቀነስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሳምንት “እናስተምር፣ እናሳውቅ፣ አሁን እንተግብር” በሚል ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል፡፡
ዘጋቢ፡ መሐመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የፍርድ ቤቶች እና የፍትህ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጥምረት የፍትህ አሰጣጥ ላይ ውጤታማ ማድረጉ ተገለጸ
አቶ ዮሐንስ አበጋ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ
የአፈር ጤናን በመጠበቅና ለምነትን በማሻሻል የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የወራቤ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።