ሀዋሳ፡ ሕዳር 14/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት በክረምት የበጎፈቃድ አገልግሎት ወቅት መከናወናቸውን ተገልጿል።
9መቶ ሺህ ብር በሆነ ወጪ የተሰራው መኖሪያ ቤት ለአንዲት አቅመ ደካማ እናት ተሰጥቷል።
አብሮነትና መደጋገፍ በሀገራችን ህዝቦች ዘንድ የተለመደ ወርቃማ እሴት እንደመሆኑ በየጊዜው በሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ጎልተው የሚታዩ የህብረተሰቡ ችግሮች እንዲቃለሉ የተቀናጀ እንቅስቃሴ ሲደረግ መቆየቱን የሀዲያ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ይርጋ ሀንዲሶ ገልጸዋል።
በሀዲያ ዞን በ2016 የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 540ሺህ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር ከ850ሺህ በላይ ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱም 12.9 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሀብት መሸፈን መቻሉን አቶ ይርጋ ተናግረዋል።
በጎነት ድንበር የሌለው፣ ጊዜም የማይለይ መልካም ተግባር ነው ያሉት የሀዲያ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምሬ ኤርሚያስ መንግስት ከባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ህይወት ለመለወጥ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
አቅመ ደካሞችን ለመርዳት የብዙ ገንዘብ ባለቤት መሆን ብቻ እንደማይጠበቅ ያነሱት አቶ ታምሬ አንዱ የሌላውን ሸክም መጋራት የሚችለው ቅን ልቦና ሲኖረው ነው ብለዋል።
በሀዲያ ዞን የሲራሮ ባደዋቾ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ አማን እንዳሉት፤ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወቅት ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀው ለ8 አቅመ ደካሞች ቤት በመገንባት ካለባቸው የመጠለያ ችግር እንዲላቀቁ ተደርጓል።
በወረዳው በሼ ገፈርሶ ቀበሌ ነዋሪ ለሆነች የ6 ልጆች እናት 9መቶ ሺህ ወጪ በማድረግ የመኖሪያ ቤት ያሰሩላት ገራድ አቶ አየለ ኤርቃሎ እንደተናገሩት፤ ለሌላው ለመትረፍና ለመርዳት ሀብታም መሆን እንደማይጠበቅና ሁሉም በመተሳሰብ መንፈስ ተቀናጅቶ ከሰራ አቅመ ደካሞችን ወደ ተሻለ የህይወት ደረጃ ማድረስ ቀላል መሆኑን ጠቁመዋል።
በበጎ ፈቃድ ወቅት አዲስ ቤት ተሰርቷላት መኖር የጀመረችው የ6 ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ ጎበኔ አዲሴ፤ ባለፉት ጊዜያት በአጥር መሳይ ቤት ውስጥ ልጇቿን ይዛ እንደምትኖር አስታውሳ አሁን ግን በባለሀብቱ እርዳታ ውብ መኖሪያ ቤት ተሰርቷላት ኑሮ በመጀመሯ ስጋት እንደሌለባት ተናግራለች።
ዘጋቢ: ዳኜ አየለ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ