የይርጋጨፌ ከተማን የኮሪዴር ልማት ለነዋሪዎች ምቹ ከተማ እንዲትሆን ከማድረግ ባለፈ የከተማዋን ገፅታ የቀየረ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር በማከናወን ላይ ያለውን የኮሪደር ልማት ለነዋሪዎች ምቹ ከተማ እንድትሆን ከማድረግ ባለፈ የከተማዋን ገፅታ የቀየረ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ።
የከተማ አስተዳደሩ ሕብረተሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ ከ17 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጿል።
በከተማዋ እየለማ ባለው የኮሪደር ልማት ዙሪያ ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች አቶ አለልኝ እምነቴ እና አቶ አሰፋ ገብረህይወት ከመልማታቸው በፊት አስቸጋሪ እና ለእይታ ምቹ ያልነበሩና የቆሻሻ መጣያ ሥፍራዎች አሁን ላይ ማራኪ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ሌሎች ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች አቶ ኤፍሬም ፀጋዬ እና ግዛው አብዲ በከተማ አስተዳደሩ ከባለፈ ዓመት ጀምሮ በመከናወን ላይ የሚገኙ የመንገድ፣ ድልድይ እና ሌሎች የኮሪደር ልማት ተግባራት አስደሳች ናቸው ብለዋል።
በመጠናቀቅ ላይ ያለው የሐምሌ 19 አደራሽን ጨምሮ ሌሎች የልማት ሥራዎች፣ ከተማዋን ያነቃቁ እና በግሉ ዘርፍ ያሉ ባለ ሀብቶች ጭምር እንዲያለሙ የሚስቡ በመሆናቸው፣ መንግስት ለኢንቨስትመንት ምቹ መደላድልን መፍጠር ይገባል ባይናቸው።
በከተማዋ በመከናወን ላይ በሚገኙ የኮሪደር ልማት ተግባራት ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ወግደረስ ሀብታሙ ኮንስትራክሽን ባለቤት እንጂነር ወግደረስ ሀብታሙ እና የመሠረት ካሳዬ ኮንስትራክሽን ፎርማን አቶ አብዮት ተስፋዬ፣ እየተከናወነ ያለው ልማት በፍጥነት እና በጥራት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እየተወጡ እንደሆነ ተናግሮዋል።
አቶ ዳዊት ታምራት የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፥ የከተማ አስተዳደሩ በኮሪደር ልማት 17 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ለማልማት አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱንና አብዛኛዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ተቀብለው ትብብር ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ አጥርም ሆነ የተነኩ ቤቶችን ፈጥነው በማፍረስ ልማቱ እንዲፋጠን የበኩላቸውን አስተዋፆ በማበርከታቸው የመጀመሪያው ምዕራፍ በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነም አመላክተዋል።
አቶ ዘርሁን አሰፋ የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ እና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ በበኩላቸው፥ የከተማ አስተዳደሩ በፕላን እንዳትመራ የነበሩ ችግሮችን ከመፍታትም ባሻገር ከተማው በዘላቂነት በተገቢ መልኩ እንዲለማ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸው፣ አሁን ላይ በህብረተሰቡ ቀና ትብብር 500 የሚያህሉ ቤቶች ፈርሰው ልማቱ በስኬት እየተሠራ እንደሆነም አመላክተዋል።
በከተማዋ አሁን ላይ ሰፊ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶች እየመጡ መሆናቸውን የተናገሩት ምክትል ከንቲባው ፣ በርካታ የከተማ ባለሀብቶችም ህንፃዎችን አስገንብተው እያጠናቀቁ መሆናቸውንና ከተማ አሰተዳደሩ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ገልፆዋል።
ዘጋቢ: አብዶ አያላ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ