የፍትህ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ በዘርፉ እየታዩ ያሉ ማነቆዎችን ማረም እንደሚገባ ተገለፀ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተጀመረውን ሀገራዊ የፍትህ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ በፍትህ ዘርፉ እየታዩ ያሉ ማነቆዎችን ማረም እንደሚገባ የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት ገለጸ።
ሪፎርሙን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክር የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በጌዴኦ ዞን ዲላ ዲላ ከተማ ተካህዷል፡፡
በውይይት መድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፖርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበባየሁ ኢሳያስ የጌዴኦ ህዝብ ጠንካራ ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ያለው በመሆኑ በመንግስታዊ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ እርካታ በማጣት ወደ ባህላዊ ሸንጎ የሚሄዱ ተገልጋዮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡
ግጭቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ቢሆንም ህዝቡ በፍርድ ቤቶችና ሌሎች የፍትህ ተቋማት ላይ ያለው አመኔታ እያደገ የማይሄድና ተገልጋዩ መሰል አማራጮችን በስፋት የሚጠቀም ከሆነ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ጠቋሚ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ምስጋና ዋቃዮ በቀጣይ ተግባራዊ የሚደረገው የፍትህ ሪፎርሙ በዘርፉ የሚስተዋሉና ህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲነሱ መነሻ እየሆኑ ያሉ ክፍተቶችን ከመሙላት አኳያ ካለው ጠቀሜታ አንጻር በአፋኝ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሳሙኤል በፍቃዱ በበኩላቸው በዳኝነትና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ እንደ ሀገር የተዘጋጀውን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ዳኞች በአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በአግባቡ አለመሥራት፣ የሙያ ክህሎት ውስንነት፣ የሥነ ምግባር ብልሹነት፣ በጥቅማ ጥቅም የመደለልና ፍትህን የማዛባት አዝማሚያዎች በዞኑ ፍርድ ቤቶች እንደ ክፍተት ከተለዩ ጉዳዮች ተጠቃሽ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
እነዚህንና ሌሎች የዘርፉን ተግዳሮቶች በመቅረፍ ህብረተሰቡ ቀልጣፋና ተደራሽ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኝ ሀገራዊውን የፍትህ ሪፎርም በተቻለ ፍጥነት ወደ ሥራ ለማስገባት በተቀናጀ መልኩ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ: ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ