የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ
ከአካባቢው የቁም እንስሳት ሐብት አንጻር ተጠቃሚነቱ እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ሁኔታውን ለመቀየር ነው ፕሮጀክቱ መተግበር የጀመረው።
በአሪና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ያለው የቁም እንሰሳት ቁጥሩን የሚመጥን ምርታማነት ዕውን ለማድረግ ዘመናዊ የአመራረት ስርአት መዘርጋት ቁልፍ ተግባር መሆኑን በመጥቀስ፤ ለዚህም ዩኒቨርሲቲው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲን ልምድ በመጋራት የተሻለ ስራ ለመስራት የተቀናጀ ፕሮጀክት ትግበራ ሂደት መጀመሩን የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኩሴ ጉድሼ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድም የሁለቱ ዞኖች አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉንም አስረድተዋል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አለሙ አይላቴ፤ በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች የተጀመረው ፕሮጀክት ዓለማ፣ ግብና አተገባበርን ያስገነዘቡበትን የፕሮጀክት ሃሳብ አቅርበዋል።
አጠቃላይ የሀገሪቱ የእንስሳት ሃብትንና ተጠቃሚነት ከአለምአቀፍ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ለውይይት ግብዓት በሚሆን መልኩ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ደግሞ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተገኙት ዶ/ር በሪሁ ገ/ኪዳን ናቸው።
በዩኒቨርሲቲያቸው የተተገበሩ ስኬታማ የእንስሳት ሀብት ልማት ስራዎችን በማሳያነት በማቅረብ፤ የእንስሳት ዝርያ በማሻሻል ውጤት ለማምጣት ሊተኮሩ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የአሪ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ የዞኖቹን ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ መድረክ መፈጠሩ ማህበረሰቡን ከሀብቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ጅማሬ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለትግበራው የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በቀጣይ ቅንጅታዊ ስራዎቻቸው የዘርፉን ችግር ለማቃለል ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ: ዳኜ ጥላሁን – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የይርጋጨፌ ከተማን የኮሪዴር ልማት ለነዋሪዎች ምቹ ከተማ እንዲትሆን ከማድረግ ባለፈ የከተማዋን ገፅታ የቀየረ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ