የመማር ማስተማር ሂደቱ የተሻለ ቢሆንም የትምህርት ግብአት እጥረት እንዳሳሰባቸው አንዳንድ ተማሪዎች ገለጹ

የመማር ማስተማር ሂደቱ የተሻለ ቢሆንም የትምህርት ግብአት እጥረት እንዳሳሰባቸው አንዳንድ ተማሪዎች ገለጹ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 13/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የመማር ማስተማር ሂደት የተሻለ ቢሆንም የትምህርት ግብአት እጥረት እንዳሳሰባቸው በዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ የጎዞ ባሙሽ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች ተናገሩ፡፡

የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት በበኩሉ የግብአት እጥረት በሁሉም ትምህርት ቤቶች የሚታይ በመሆኑ በዘላቂነት ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

የመማር ማስተማሩ ተግባር የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊ የትምህርት ግብኣት ማሟላት ተቀዳሚ ተልዕኮ መሆኑን አስታውሰዋል።

ይሁንና በዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ የጎዞ ባሙሽ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተግኝተን ያነጋገርናቸው በርካታ ተማሪዎች እንደሚሉት በትምህርት ቤታቸው ለትምህርት ግብአት የሚሆኑ በርካታ ነገሮች አልተሟሉም።

ይህንን ከተማሪዎች መካከል ተማሪ ሜሮን ተክለ ማርያም፣ አንዷለም ባላ እና ፌቬን ይስሀቅ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መሆናቸውን ጠቁመው፥ በትምህርት ቤታቸው ከመማሪያ መጽሐፍት ጀምሮ ኮምፒዩተር፣ ቤተ ሙከራ፣ የተደራጀ ቤተ መጽሐፍት እና ሌሎችም ለትምህርት አጋዥ የሆኑ ነገሮች አለመኖራቸውን ገልጸዋል።

ተማሪዎቹ አብዛኛውን ጊዜ በመምህሩ ገለጻ ላይ ብቻ ተንጠልጥለው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉና በተግባር የተደገፈ የሳይንስ ትምሀርቶችን እንዳልተማሩም ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን ፈተና ለመፈተን የሚያስችል በቂ ዕውቀት አግኝተው እንዳይፈተኑና  በውጤታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚፈጥርም ጭምር ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቱ ከሚገኙ መምህራን መካከል መምህር አብነት ኃይለ ማርያም እና መምህር ይስሀቅ ፎላ በሰጡት የጋራ አስተያየት በትምህርት ቤቱ አጋዥ የሆኑ ግብአቶች ባይሟሉም ተማሪ በቂ እውቀት እንዲያገኝ ያላሰለሰ ጥረት በየግላቸው በማድረግ ላይ ናቸው።

በእጅ ስልካቸው መረጃ በማውረድ፣ ትርፍ ሰአት በማስተማር እንዲሁም በአከባቢው የሚገኙት ነገሮችን እንደግብአት በመጠቀም  ለተማሪዎቹ በቂም ባይሆን የተሻለ እውቀት እያስጨበጥን እንገኛለን ሲሉ መምህራን ተናግረዋል ።

የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር ኤልያስ በፈቃዱ በበኩላቸው በትምህርት ቤቱ የመምህራን እጥረት አሁን ላይ ባይኖርም ሌሎች አጋዥ ግብአቶች አለመኖራቸውን ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ አብዛኛውን የመማር ማስተማር ተግባር የሚተገብረው በህብረተሰብ ተሣትፎ መሆኑን አክለው የገለጹት ምክትል ርዕሰ  መምህሩ አስፈላጊውን ግብኣት እንዲያሟላ ለትምህርት ቤቱ ተጨማሪ ገቢ ባለመኖሩ የሚመለከታቸው አካላት እገዛ እጅግ እንደሚያሻው ተናግረዋል ።

የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ መምህር ባንተይዋል ፎላ በወረዳው ባሉት አራት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሌሎችም ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሥራ አጋዥ የሆኑ የግብአት ችግሮች ቢኖሩም አዲስ በተመሠረቱ ትምህርት ቤቶች ችግሩ ጎልቶ ይታያል ብለዋል ።

ችግሩ በዘላቂነት ለመፍታት ከዞንና የልማት አጋሮችን እንዲሁም ኅብረተሰቡን በማስተባበር ተግባሩ ተለይቶ እየተሠራ ይገኛል።

በተጨማሪም የተበላሹት ኮምፒዩተሮችና መሰል ነገሮችን በማስጠገን እንዲሁም መጽሐፍት በተመለከተ አሳታሚዎች በአስቸኳይ እንዲያደርሱ ወደመግባባት ደረጃ መደረሱን የጽህፈት ቤት ሃለፊ ተናግረዋል ።

ዘጋቢ፡ አሸናፊ ግዘው – ከዋካ ቅርጫፍ