በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ

በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 12/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው በባስኬቶ ዞን የላስካ ከተማ አስተዳደር ገለጸ።

የላስካ ከተማ አስተዳደር ከተማ አቀፍ የልማት፣ መልካም አስተዳደርና የህዝብ ንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

የላስካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር አንለይ ወንድፍራው እንደተናገሩት፤ የላስካ ከተማ ከወቅቱ ጋር እኩል እየዘመነች የምትጓዝ ከተማ እንድትሆን ንቁ የህብረተሰብ ተሳትፎ ያስፈልጋል።

ከንቲባው በ2017 የሚከናወኑ ዝርዝር ተግባራትን ዕቅድ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በቀረበው እቅድ ዙሪያና ከዚህ ቀደም ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ በተሳታፊዎች ሐሳብ አስተያየት ተሰጥቶበታል።

የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪና የዞኑ አስተዳዳሪ ተወካይ ኢንጂነር ዘማች ካንሶ በበኩላቸው፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ተቀናጅቶ በመፍታት የብዙ ፀጋ ባለቤት የሆነችውን ከተማን ካደጉ ከተሞች ተርታ ማሰለፍ ይገባል ብለዋል።

በውውይቱ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ም/ኃላፊና አስተዳደርና ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ገሌቦ፤ በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ የህዝብ ልማት ተሳትፎን በማጠናከርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ችግሩን በመለየትና ዘላቂ መፍትሄ በማስቀመጥ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ከተማውን የሚመሩ አካላት የሚያቅዷቸውን እቅዶች ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ለማስቻል በቂ ጊዜ ተሰጥቷቸው ተረጋግተው እንዲሰሩ አለማድረግና ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ጽዱ እና ምቹ ለማድረግ የአካባቢን ንፅህና ለማስበቅ በሚደረገው ጥረት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዳሉ ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።

የተለያዩ የመሠረታዊ ልማቶች አቅርቦት ዙሪያ በተለይም በህዝቡ ዘንድ የረዥም ግዜ ቅሬታ ሆኖ የቆዬው የላስካ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ግንባታ መቋረጥ በሰፊው ጥያቄ ተነስቷል።

በከተሞች የሚፈጸሙ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራዎችንና በአገልግሎት አሰጣጥ መነሻ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን በጋራ ከመከላከል አኳያም ከተነሱ አንኳር ሀሳቦች መካከል ናቸው።

ስራ ፈላጊውን ወጣት አደራጅቶ በየሙያ መስኩ ወደ ሥራ ለማስገባትም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባም በውይይቱ ተሳታፊዎች ተጠቁሟል።

ውይይቱን ከመሩ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

በተቋማት የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን ከማጋለጥ አንስቶ የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አንስተው በተለይ በመሬት ዙሪያ የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች ልዩ ክትትል እንደሚሹ የላስካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር አንለይ ወንድፍራው ገልጸዋል።

የተሰሩ መሠረተ ልማቶችን ተፈላጊውን አገልግሎት እንዲሰጡ እና የሚሰበሰቡ ገቢዎችን በተገቢው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማስቻል ህብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋፅዖ ማበርከት እንደሚገባው ጥሪ አቅርበዋል።

የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪና የዞኑ አስተዳዳሪ ተወካይ ኢንጂነር ዘማች ካንሶ፤ በህግ ሽፋን የሚፈጸሙ ስርቆቶችን መርምሮ እርምጃ በመውሰድና በተለያዩ ጉዳዮች የተሰበሰቡና ስራ ላይ የዋሉ ገንዘቦች ሪፖርት መዘግየት ለመቅረፍ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን