ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ

ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 12/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ የቡርጂ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ጠቁሟል፡፡

መምሪያው በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እና ስነ-ምግባር ዙሪያ የግንዛቤ ሥልጠና ለባለድርሻ አካላት ሰጥቷል።

የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የቡርጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ኮሬ አዶ፤ ሚዲያ ለሀገር ገፅታ ግንባታ ያለውን ጥቅም በመረዳት በአግባቡ መጠቀም አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

በቡርጂ ዞን ያለውን እምቅ ሀብት ለዓለም ለማስተዋወቅ እና ልማቱን ለማፋጠን ሚዲያዎች ወሳኝ መሆናቸውን ተረድተን ለበጎ ዓላማ ብቻ ማዋል እንደሚገባ አክለዋል።

የቡርጂ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን መመሪያ ኃላፊ አቶ አቤል አይላ እንዳሉት፤ ሚዲያ በአግባቡ ከተመራ እድገትን የሚያፋጥን፣ በአግባቡ ካልተመራ ደግሞ አጥፊ መሣሪያ መሆኑን ተረድተን በኃላፊነት እና በተጠያቂነት መንፈስ በጥንቃቄ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል።

በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ውስጥ የማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያ የሆኑት በአቶ ደጀኔ ፈጠነ የተዘጋጀው ሚዲያ ያለው ጥቅምና ጉዳት እንዲሁም የሚዲያ አማራጮችን ተጠቅመን በዞኑ የሚገኙ ሀብቶችን የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት እንደሚገባ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃዎችን በመቆጣጠር ለአካባቢው መልካም ገፅታ ግንባታ መጠቀም ያስፈልጋልም ብለዋል።

በግንዛቤ መስጫ መድረኩ በሶስቱም መዋቅሮች የሚገኙ የሚዲያ ባለሙያዎች እና አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

ዘጋቢ: ወርቅአገኘሁ ወልደየስ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን