የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 12/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት በክልሉ ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ያስችላል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በኣሪ ዞን ጂንካ ከተማ የኤሶል ልዩ 2ኛ ደረጃ አዳሪ ት/ቤት የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደስ በተገኙበት ተመርቆ ተከፍቷል።
የኣሪ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳግም መኮንን እንደገለፁት እንደ ሀገር የገጠመንን የትምህርት ስብራት ለመጠገን በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት እየተተገበሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች መሆኑን ገልፀው፥ ትምህርት ቤቱ ለዚህ እንዲበቃ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው ትምህርት ለሁለንተናዊ ለውጥ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን በማመን ከወላይታ ሊቃ ት/ቤትና ከአርባምንጭ ባይራ ት/ቤት ተሞክሮ በመውስድ ለዚህ መብቃቱን አስታውሰዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ እንዲህ አይነት አዳሪ ት/ቤቶች ለክልላችን ህዝቦች ትልቅ አቅምና ዕድል መሆኑን ተናግረው በሁሉም አከባቢ እንዲህ አይነት አዳሪ ት/ቤቶች ሊስፋፉ እንደሚገባና ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አክለውም በአለም ለመወዳደር ዕውቀትን መሠረት ያደረገ፤ ችግር ሊፈታ የሚችልና ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችልና የነበሩ የትምህርት ስብራቶችን በምጠገን ከደህነት ልንወጣ የሚገባን ቁልፍ መሳሪያ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ ለዚህ ምረቃ እንዲበቃ አስተዋጽኦ ላደረጉ የአከባቢው ማህበረሰብና ሌሎችም አካላት ኃላፊው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም የተለያዩ ወረዳዎችና ተቋማት ለትምህርት ቤቱ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርገዋል።
ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ከተማዋ ፅዱና ውብ እንድትሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ነው – የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/