የትምህርት ጥራትና ውጤት መሻሻል ዙሪያ የሚተገበሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ አሳሰበ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 12/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የትምህርት ጥራትና ውጤት መሻሻል ዙሪያ የሚተገበሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ አሳስበዋል።
በኣሪ ዞን ኤሶል ልዩ 2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት መርቀው ወደ ሥራ ባስገቡት ወቅት ነው ዶ/ር አበባየሁ ይህንን ያሳሰቡት።
አዳሪ ትምህርት ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ9ኛ ክፍል 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን አሀዱ ብሎ መጀመር የሚያስችል ፕሮግራም ተካሂዷል።
የበጀት ዓመቱ የመማር ማስተማር ሥራውን ባሉበት ትምህርት ቤት ሲከታተሉ ቆይተው አዳሪ ትምህርት ቤቱ ያወጣውን ፈተና ተቀብለው ወደ ማዕከሉ እንዲገቡና ከህዳር 13/2017 ዓ.ም ጀምሮ የክፍል መማር ማስተማር ሥራው እንዲጀመር ዝግጅት መደረጉን የኣሪ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ዳግም መኮንን ገልፀዋል።
የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው፤ ትምህርት የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን ጠቁመው በዘርፉ እንደ ሀገር ወጥ የሆነ ውጤት መመዝገብ እንዲችል ዞኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
ዞኑን፣ ክልሉንና ሀገርን ጠቅሞ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ዜጎችን ለማፍራት ዞኑ ልዩ 2ኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ማቋቆሙን ዋና አስተዳዳሪው ገልፀዋል።
ተቋሙ በግብዓትና አጠቃላይ አደረጃጀት የተሟላ ሆኖ አገልግሎት እንዲሰጥ ሁሉ አቀፍ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት አቶ አብርሃም አመስግነዋል።
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ፤ በክልሉ የሚገኙ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ቁጥር ውስን በመሆኑ በሁሉም አካባቢ ይህ ተግባራዊ እንዲደረግ ጠንክሮ መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል።
ዓለምን የሚናይበት መነፅር፣ በአጠገብ ያለውን ሀብት አውቆ ለመጠቀም ትምህርት ግንባር ቀደም ተግባር በመሆኑ መላው ህዝብ ለትምህርት ልማት ርብርብ እንዲያደርግ ዶ/ር አበባየሁ ጥሪ አቅርበዋል።
ትምህርት ላይ ትኩረት ሰጥተን ድህነትን ለማስወገድ መሥራት አለብን፤ ልጆቻችን ጠንካራ መሠረት ላይ እንዲቆሙ እንሥራ ሲሉም ዶ/ር አበባየሁ አሳስበዋል።
ታዳሚዎች በተቋሙ በመዘዋወር አገልግሎት ሰጪ ክፍሎችን ጉብኝተዋል።
ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
በትምህርት ሴክተር የመረጃ አያያዝ ውጤታማነት ዙሪያ በኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በትምህርታቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋና ቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ