ከ11ሺህ አምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ህፃናት የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል
ሀዋሳ፡ ሕዳር 12/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከ11ሺህ አምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ህፃናት የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት አስታውቋል።
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ክትባት ዘመቻ ከህዳር 09/2017 ዓ.ም ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ ዶክተር ፀጋዬ ሻሜቦ እንደገለፁት፤ የማህፀን በር ጫፍ ከንሰር “ሁማን ፓፕሎማ” በተሰኘ ቫይረስ የሚመጣና ሴቶችን የሚያጠቃ ሲሆን ክትባቱ በኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ይገኛል።
የክትባት ዘመቻው ከህዳር 09/2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 13/2017 ዓ.ም ባሉት አምስት ተከታታይ ቀናት በአብዛኛው በትምህርት ተቋማትና ሌሎችም ስፍራዎች እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በልዩ ወረዳው ከ11ሺህ አምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ህፃናት ክትባቱን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ህብረተሰቡ በሽታውን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች የጋራ ግንዛቤ በመያዝ እድሜያቸው ከ9-14 ባለ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን ወደ ክትባት ዘመቻ ስፍራዎች በመላክ ማስከተብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት የእናቶችና ህፃናት ጤናና ስርዓተ ምግብ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ወንድሙ ወቼቦ በበኩላቸው፤ ከክትባት ዘመቻው ጎን ለጎን የሴቶችንና የህፃናትን የስርዓተ ምግብ ሁኔታ የማጥናት ስራዎችን እየተሰራ እንገኛለን ብለዋል።
ከተለያዩ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ እቅድ በማውጣት ስራው መጀመሩን ጠቁመው ለልጅ አገረዶች በትምህርት ተቋማት ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች ተሰርተው ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
በጤና ኤክስቴንሽኖችና ባለሙያዎች ክትባቱ እየተሰጠ እንደሚገኝ በመጠቆም።
በልዩ ወረዳው ያነጋገርናቸው ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ወ/ሮ አስናቀች ሀደሮ እና አማረች አሰሌ በበኩላቸው፤ ልጅ አገረዶች ስለ ክትባቱ ግንዛቤ ተፈጥሮላቸው የክትባት ዘመቻውን በአግባቡ እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የጤና ባለሙያዎች በኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ
የባስኬቶ ዞን ተወላጆች የአንድነት መድረክ ማጠቃለያ እየተካሄደ ነው
በእንስሳት እርባታ ከተሰማራን ወዲህ ኑሯችን ተሻሽሏል – የጋዘር ከተማ ወጣቶች