በመኸር የእርሻ ወቅት ከለሙ ዋና ዋና ሰብሎች የታቀደውን ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው
ሀዋሳ፡ ሕዳር 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በመኸር የእርሻ ወቅት ከለሙ ዋና ዋና ሰብሎች የታቀደውን ምርት ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መሆኑን በዳውሮ ዞን የማረቃ ወረዳ አርሶአደሮች ገለጹ፡፡
የወረዳው ግብርና ደን አከባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ ጽ/ቤት በበኩሉ በመኸር እርሻ ወቅት ከለማው ከ8 ሺህ ሄክታር በላይ ማሣ ከ2 መቶ ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብሏል።
በመኸር እርሻ ወቅት ጤፍ፣ ስንዴ፣ አተር፣ ባቄላ እና ሌሎችም ዋና ዋና ሰብሎች በስፋት የተመረቱ ሲሆን አሁን ላይ የደረሱ ሰብሎች እየተሰበሰቡ ይገኛሉ።
ከአምራች አርሶአደሮች መካከል አርሶአደር ተስፋዬ ፎላ፣ አበበ አሻንጋ፣ ታምራት ታዬ እና ሌሎችም አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት ማሣቸውን አለስልሰው በማረሳችን፣ ምርጥ ዘርን ጨምሮ ሙሉ የግብርና ፓኬጅ በመጠቀማችን በአሁኑ ወቅት በማሳችን ላይ የተሻለ ምርት እያየን እንገኛለን ብለዋል ።
ባለፈው ወር ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ተከታትሎ በመዝነቡ ምክንያት ስጋት ላይ መውደቃቸውን የገለጹት አርሶአደሮቹ አሁን ዝናቡ ጋብ በማለቱ የደረሱት ሰብሎችን በማጨድ፣ ያልደረሱትን ደግሞ የአረም ቁጥጥር እያደረጉ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል ።
አርሶአደሮቹ እንደሚሉት የግብርና ባለሙያዎች እገዛ አልተለያቸውም። ሰብሉ በዋግና መሰል የሰብል በሽታዎች እንዳይጠቃ የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት የመድኃኒት እርጭት ማድረጉ ለምርቱ ማማር የራሱን ሚና እንደተወጣ አብራርተዋል።
በወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ከሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች መካከል አቶ ግርማ ሀይሌ በመኸር እርሻ በሁሉም ቀበሌያት የአካባቢውን ሥነ ምዕዳር መነሻ በማድረግ የሚፈልገው ሰብል እንዲዘራ ተደርጓል ብለዋል ።
አርሶአደሮቹ የሚፈልጉት ምርት እንዲያገኙ በእርሻ ሥራ ወቅት ሁሉ አስፈላጊውን ሙያዊ እገዛ በማድረጋችን ማሳ ላይ ተስፋ ሰጪ ምርት እየታየ ይገኛል።
በተለይ ለአጨዳ ያልደረሱ ሰብሎችን የአረም ቁጥጥር እንዲያደርጉ ክትትልና ቁጥጥር እንዳልተለየ ጨምረው ተናግረዋል።
የማረቃ ወረዳ ግብርና፣ ደን፣ አከባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ወርቁ እንደገለፁት በመኸር እርሻ 8 ሺህ 327 ሄክታር መሬት በዋና ዋና ሰብሎች መሸፈኑን ጠቁመው፥ ከዚህም 230 ሺህ ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃልም።
በአሁኑ ሰዓት እንደ ጤፍ ያሉ የደረሱ ሰብሎች 80 በመቶ መሰብሰባቸውን ገልጸው በማሣ ላይ ያሉት በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በቀሪው ወራት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የደረሱ ሰብሎችን አርሶ አደሩ ተዘናግቶ እንዳያወድም ተገቢ ድጋፋዊ ክትትል እየተደረገ ይገኛል።
ዘጋቢ : አሸናፊ ግዛው – ከዋካ ጣቢያችን
More Stories
ከህዝቡ ለሚነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተጠቆመ
የተያዙ ግቦችን በአግባቡ በማከናወን አብዛኞቹ ተግባራት ማሳካት መቻሉን የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አስታወቀ
በሕብረተሰቡ የሚነሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ