የ40 ዓመታትን  ቂም በቀል የሻረው የጎፋዎች የእርቅ ማዕድ  የ”ባራንቼ ዎጋ” ስርዓት

በጎፋ ዞን ለ40 ዓመታት በቂም በቀል የሚፈላለጉ ጎሳዎች በፍቅር ተገናኝተዋል ፡፡

ለ40 ዓመታት በቂም በቀል የሚፈላለጉ ጎሳዎች በባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት በፍቅር ተገናኝተዋል።

ከፍትህ ስርዓቱ ጎን ለጎን ባህላዊ የእርቅ ስርዓት እየተበራከተ የመጣውን የወንጀል ድርጊቶችን ከመቀነስና ከመከላከል አኳያ ፋይዳው የጎላ ነው።

በጎፋ ዞን ዑባ ደብረ ጸሐይ ወረዳ “ሼለካዎና” ጎሳ እና  “ካላታ” ጎሳ አባላት መካከል  በድንገተኛ የሰው ግድያ ምክንያት በቂም በቀል ለ40 ዓመታት እርስ በእርሳቸው ለመጠፋፋትና ለበቀል ሲፈላለጉና ሲጠባበቁ የነበሩ ቤተሰቦች በጎሳ መሪዎች በባህላዊ ዕርቅ ስነ-ስርዓት ቤተሰብ ሆነዋል።

በሁለቱ ጎሳዎች ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በአከባቢው ባህላዊ የእርቅ ዘዴ በሆነው “ባራንቼ ዎጋ” ስርዓት ተፈቷል።

በሁለቱ ጎሳዎች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ከ40 ዓመታት በላይ በማህበራዊ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ከማሳደሩ ባሻገር በአካባቢው የሰላምና ፀጥታ ስጋት ሆኖ ቆይቷል።

የዑባ ንጉስ (ካዎ) ማዳን ጨምሮ  ባቦዎች ፣ ከተለያዩ ጎሳዎች የተወጣጡ የማህበረሰብ ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የባህል መሪዎች  ጥላቻን በፍቅር፣ ቂምን በይቅርታ፣ ግጭትን በውይይት፣ ጭካኔን በደግነት እንዲለወጥ  በእርቁ ወቅት ሚናቸው የላቀ ነበር።

በዑባ የላ ቀበሌ በሁለቱ ጎሳዎች መካከል የተፈጸመውን እርቅ ተከትሎ ከሶስት ወር በኋላ በየላ ሻቦ ቀበሌ የተበዳይ ቤተሰቦች ሰርግ ደግሰው የበዳይ ቤተሰቦችን ጠርተዋል።

በርካታ የበዳይ ቤተሰቦች 20 ኪሎ ሜትር አቋርጠው ስጦታ ይዘው ለበዳይ ቤተሰቦች ብቻ አቀባበል ተብሎ በተዘጋጀው ሰርግ ተገናኝተዋል።

በደስታ ተቃቅፈዋል መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል ማዕድ ተጋርተዋል። በጋብቻ ምክንያት ከአከባቢው የተለዩ ዘመዳሞች ተገናኝተዋል። አሁን የሁለቱ ጎሳ አባላት ሰላማቸው ተረጋግጦ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ተመልሰዋል።

የሁለቱ ጎሳዎች አባላት በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት በጋብቻ፣ በለቅሶ፣ በሕዝባዊ የውይይት መድረኮች እንደማይሳተፉና በማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ አሉታዊ ጫና እንዳሳደረባቸው ያነሳሉ።

የበዳይ ቤተሰብ አባላት የሆኑት አቶ አካሉ አንቦ እና ወ/ሮ አለሚቱ ጫልጋ እንደተናገሩት፤ ላለፉት 40 ዓመታት የበቀል እርምጃ ይወሰድብናል በማለት ከህጻንነታችን ጀምሮ በሰፈራችን፣ በትምህርት ቤት፣ በስራ ቦታና የተለያዩ ማህበራዊ ሁነቶች በሚከናወኑ ቦታዎች በስጋትና በጥርጣሬ ኖረዋል።

አሁን ለተፈጠረው ሰላምና ፍቅር የባህል መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የተበዳይ ቤተሰቦች ምስጋና ይገባቸዋል።

ሰው ከሰው ጋር ከታረቀ ፈጣሪም ከሰው ልጆች ጋር ይታረቃልና ፈጣሪያችን በሰጠን ዕድሜ መልካም መልካሙን በመስራት በይቅርታና በፍቅር የተሞላ ስብዕና ተላብሰን ለሌሎች ምሳሌ መሆን ይገባናል።

የተጣላ በመታረቅ የሰላምና እርቅ መንገድንም በመምረጥ በመካከላችን ወንድማማችነትን ለመፍጠር ይቅር ተባብለናል የሚሉት የተበዳይ ቤተሰብ አባላት የሆኑት አቶ ኢትዮጵያ ቶጶ እና አቶ ሳሙኤል ቶይሳ ናቸው።

ለሰላም የተዘረጋውን እጅ  በደስታ መቀበል ትርፋማ ያደርጋል ነው ያሉት።

በይቅርታ እና በፍቅር እንጂ በጥላቻ እና በቂም በተሞላ ስብዕና ምንጊዜም ሰላማዊ ህይወት ሊኖረን አይችልም ሲሉ ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታትና ቤተሰባዊ ግንኙነትን ለመፍጠር ባህላዊ የግጭት አፈታት መንገዶችን መጠቀም ይገባል።

በአከባቢው የባህል መሪ ከሆኑትና በማስታረቁ ተግባር ከተሳተፉት መካከል ባቦ ዱዳ ኩኛከ ኩማ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓትን በመጠቀም ቂምና በቀልን በመተዉ በአብሮነት መንፈስ ወደ ነበረበት ሠላምና ከእርስ በእርስ መፈላለግና ከጥርጣሬ ወጥተው ሰላማዊ ህይወት እንዲመሩ በማሰብ ዕርቁን ማስፈጸማቸውን ያወሳሉ።

ባህላዊ የግጭት አፈታት መንገዶችን በመጠቀም በአካባቢው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታትና ቤተሰባዊ ግንኙነትን ለመፍጠር በዞኑ በትኩረት እየተሰራ ነወ።

የጎፋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ድንበሩ ደርቤ በበኩላቸው፤ በዞኑ ሰላምና አብሮነትን ለማስቀጠል ህብረተሰቡ የቆየውን ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴዎችን በመጠቀም ችግሮችን እንዲፈታ በዛላና ዑባ ደብረጸሐይ ወረዳዎች በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል።

ጥላቻ መለያየትን፣ ግጭትን እና መከራን ሊፈጥር ይችላል፣ ይቅርታ ግን ቂምን ትተን ወደ ፊት እንድንራመድ ያስችለናል ባይ ናቸው። ለዚህ ደግሞ “የጎፋ ባራንቸ ወጋ” አበርክቶ የላቀ ስለመሆኑ ያነሳሉ።

የአካባቢ ሰላምና ጸጥታ ለመጠበቅና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የቀደምት አባቶች ሀብት የሆነው ባህላዊ  የእርቅ ስነ-ስርዓት ተጠናክሮ ይቀጥል መልዕክታችን ነው።

አዘጋጅ፡  አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን