ከህዝቡ ለሚነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከህዝቡ ለሚነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በአሪ ዞን የጂንካ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡
ከተማ አቀፍ የህዝብ ውይይት መድረክ በዞኑ ጂንካ ከተማ ተካሂዷል።
መድረኩን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሠ፤ የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታና የጂንካ ከተማ ከንቲባ ከቶ ሲሳይ ጋልሺ በጋራ መርተዋል።
በከተማው የሚሰሩና እየተሰራ ያለውን የልማት ስራ የከተማው ከንቲባ አቶ ሲሳይ ጋልሺ ለተሳታፊዎች በዝርዝር አቅርበዋል።
ከተማውን አቋርጦ የሚያልፈውና በፌደራል መንግስት የሚገነባው አስፓልት መንገድ ሥራ የጥራት ጉድለት፣ የኑሮ ውድነት፣ በከተማው ማስፋፊያ የተካተቱ ቀበሌያት የመሠረተ ልማትና የማስተር ፕላን ጥያቄ ምላሽ ማጣትና ሌሎች በርካታ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱ ስሉ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል፡፡
በበጀት አመቱ በተለይ በትምህርትና ጤና እንዲሁም ለወጣቱ እየተፈጠረ ያለውን የሥራ እድል ያብራሩት የጂንካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሲሳይ ጋልሺ የውስጥ ለውስጥ መንገድ እና አነስተኛ ድልድይ ሥራዎች እንዲሁም ከተማዋና ከሌሎች አጎራባች ከተሞች የሚያገናኙ መንገድ ስራዎችን ከፌደራል እና ከክልል መንግስት ጋር ታቅዶ እየተሰራ እንዳለ አመላክተዋል።
ማህበረሰቡ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በመደገፍና በመሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ ህገ ወጥ ተግባራትን በማጋለጥ የድርሻውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በመድረኩ የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ እንደገለፁት የጂን ከተማ የዞኑ እና የክልሉ ማህበራዊ ክላስተር መቀመጫ እንደመሆኗ ለከተማው እድገት ዞኑ የክልል እና የፌድራል አካላትን በማስተባበር በቅርበት የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።
የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ጉዳዮችንም ለመቅረፍ ለከተማ አስተዳደሩ ልዩ ድጋፍ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሠ የከተማውን ዕድገት ለማፋጠን የመንግስት አካላት ከሚሰራው በተጨማሪ ማህበረሰቡ በተለይ ገቢና ቀረጥን በታማኝነት መክፈልና መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
ከመዋጮና አንዳንድ ድጋፎች በተጨማሪ ወደ ከተማው የሚመጡትን ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ በማራዘም ተጨማሪ የገቢ አማራጭ ለማድረግ መስራት ይጠይቃል ያሉት ዶ/ር አበባየሁ፥ በመሠረተ ልማት እና አንዳንድ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት ከተጠያቅነት ጋር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በውይይቱ የሀገር ሽማግለዎች፤ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች፤ የወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀት ተወካዮች፤ ዙሪያ ቀበሌያት ተወካዮች እና ልዩ ልዩ ማህበራዊ መሠረትን የወከሉ አካላት ተገኝተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
በመኸር የእርሻ ወቅት ከለሙ ዋና ዋና ሰብሎች የታቀደውን ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው
የተያዙ ግቦችን በአግባቡ በማከናወን አብዛኞቹ ተግባራት ማሳካት መቻሉን የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አስታወቀ
በሕብረተሰቡ የሚነሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ