በሕብረተሰቡ የሚነሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሕብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባ በጌዴኦ ዞን ጨለለቅቱ ከተማ አስተዳደር ገልጿል፡፡
አስተዳደሩ የከተማ ልማትና መልካም አስተዳደር ዙሪያ የተዘጋጀ የሕዝብ ንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጨለለቅቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተስፋዬ ፈይሳ እንደተናገሩት፤ በሕብረተሰቡ ዘንድ አብዛኛውን ጊዜ ቅሬታ የሚያስነሱ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን በቁርጠኝነት ወደ መሥራት መገባቱን አመላክተዋል።
የጨለለቅቱ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ የከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሕንጻ፣ የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ጽሕፈት ቤትና፣ የከተማ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ በዘርፉ በተደረገ ከፍተኛ ርብርብ በአሁኑ ሰዓት ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል ነው ያሉት።
በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቱ እያካሄደች ያለውን የከተሞችን የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በማፋጠን ሕብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ያላሰለሱ ጥረቶች መኖራቸውን ጠቁመው ባለድርሻ አካላት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የጌዴኦ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ምክትል ኃላፊና የቤቶች ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አክሊሉ በደቻ በበኩላቸው፤ ከተማን ለነዋሪዎች ማራኪና ምቹ ለማድረግ፣ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንደሚገባው አብራርተው ከማስተር ፕላን ውጪ የሚከናወኑ ሕገ-ወጥ ግንባታዎችንና የመሬት ወረራ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል ይገባል ብለዋል።
በኮሪደር ልማት ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሀገሪቱ ብሎም የፓርቲው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የገለጹት የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ አበባየሁ ኢሳይያስ ልማቱን ማስፋፋት የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ መንግስት በዘርፉ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ከተማውን ለማልማት በሚደረገው እንቅስቃሴ ነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት እያደረጉ ያሉት የልማት ተነሳሽነትና ትብብር አበረታች መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ከመንግሥት ጎን በመቆም በማናቸውም ልማታዊ ሥራዎች ላይ የነቃ ተሳትፏቸዉን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘብዴዎስ ኤካ በበኩላቸው፤ ጥራቱን የጠበቀ ፈጣን አገልግሎት ለተገልጋዮች ለመስጠትና በየደረጃው የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለማረም በዘርፉ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት መፍታትና የመፈጸም አቅምን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
የከተሞቻችን የእድገት ፍጥነት የሚመጥን ዕቅድ ማቀድና በጋራ መፈጸም እንደሚያስፈልግ ያስረዱት አቶ ዘብዴዎስ በከተማው ልማት ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ መልካም አስተዳደርን ማስፈንና ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡ እስራኤል ብርሃኑ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
እርስ በርሳችን ከመቃቃር ይልቅ አንድነታችንን በሚያጠናክሩ ሀሳቦች ላይ ትኩረት በማድረግ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ከተማና ወረዳ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤቶች አሳሰቡ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ገለጹ
ከኑሮ ውድነትና ከኢኮኖሚ ችግር ለመላቀቅ ያሉንን ፀጋዎች በአግባቡ በመጠቀም መስራት እንደሚያስፈልግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ገለፀ