የሕብረተሰቡን የፍትህ ተደራሽነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የኣሪ ዞን ምክር ቤት አስታወቀ

የሕብረተሰቡን የፍትህ ተደራሽነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የኣሪ ዞን ምክር ቤት አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ፍርድ ቤቶችና የፍትህ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የሕብረተሰቡን የፍትህ ተደራሽነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የኣሪ ዞን ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት በኣሪ ዞን የፍርድ ቤቶች የፍትህ ተቋማት ሪፎርም ሥራዎች ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ በጂንካ ከተማ ተከናውኗል፡፡

የኣሪ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ስመኝ ተስፋዬ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፍርድ ቤቶችና የፍትህ ተቋማት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የአገልግሎት አሰጣጥን በመዘመን የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የኣሪ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ በበኩላቸው፤ የንቅናቄው መድረክ በፍትህ ተቋማት ላይ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ስለሚያግዝ ባለድርሻ አካላት ትኩረት በማድረግ የለውጥ ፕሮግራሞችን በቁርጠኝነት ሊመሩ ይገባል ብለዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም ሀገር በቀል የአለመግባባት መፍቻዎችን በመጠቀም ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ለፍትህ ስርዓቱ ተገቢውን ሚና እንዲወጣ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

ለመድረኩ ተሳታፊዎች በኣሪ ዞን  ፍትህ መምሪያ  ኃላፊ አቶ ደምሴ ላልሲ እና የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አቶ አንተነህ በላይ ሰነድ ቀሪቦ በተሳታፊዎች ውይይትም ተደርጓል፡፡

ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከጂንካ  ጣቢያችን