የከተሞችን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ የህዝቦች የላቀ ተሳትፎ ያሻል –  ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገ/መስቀል ጫላ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የከተሞችን ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ የህዝቦች የላቀ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገ/መስቀል ጫላ ተናገሩ።

ም/ርዕሰ መስተዳድሩ በአርባ ምንጭ ከተማ የተጀመረውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ መድረክ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት ነዋሪዎች በየአከባቢያቸው ምቹ የልማትና የመልካም አስተዳደር ይረጋገጥ ዘንድ የዜጎች ተሳትፎ የላቀ ነው ብለዋል።

የአርባምንጭ ከተማ በህዝቦቿ ሁለንተናዊ ድጋፍ ያረጋገጠቺውን ሠላም ማስቀጠል ትልቅ ስራ ነው ያሉት ም /ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በከተማዋ ያለውን ከፍተኛ የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ መንግስት ጥረት ያደርጋል ብለዋል።

በከተሞች የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ጫናን ለማቃለል ጥረቶች መጀመራቸውን የተናገሩት አቶ ገ/መስቀል በዘርፉ ውጤት ይመጣ ዘንድ የህዝቡና የመንግስት የጋር የቤት ስራ ነው ብለዋል።

አሁን አሁን የመንግስት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ስርአቱ አደጋ ላይ መሆኑን ተከትሎ መንግስትና ህዝብ በጋራ ችግሮችን በመለየት ለመፍትሄው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን የምታስተናግደው የአርባ ምንጭ ከተማ የሚመጡ እንግዶችን በጨዋነት ተቀብሎ ማስተናገድ እንዲችልም በክልሉ መንግስት ስም ጥሪ አቅርበዋል።

የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ በበኩላቸው ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹና ፅዱ ለማድረግ የውስጥ ለውስጥ መንገድን ጨምሮ የኮሪደር ልማቶች በተጠናከረ መንገድ እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

የት/ቤቶችና የጤና ተቋማት ግንባታ የህዝቡን ቁጥር በሚመጥን መልኩ እየተገነቡ መሆናቸውን ያስታወሱት ከንቲባው የዞኑን እምቅ የስፖርት አቅምን ለማጉላት የሚያስችል አለም አቀፍ የስታዲየም ግንባታም እየተከናወነ ስለመሆኑ አውስተዋል።

ከተማዋ ካላት ፈጣን እድገት አኳያ ከፍተኛ ህገ-ወጥ  የመሬት ወረራ መኖሩን የተናገሩት አቶ ገዛኸኝ ይህንን ፈር ለማስያዝም ህጋዊ ርምጃ እየተወሰደ ስለ መሆኑም ጠቁመዋል።

በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ባለው የከተማ የመልካም አስተዳደርና የልማት ስራዎች የንቅናቄ መድረክ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች፣ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉበት ይገኛል።

ዘጋቢ: በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን