የውስጥ ገቢ አሰባሰብ ሥርዓትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተገለጸ

በበጀት ዓመቱ የውስጥ ገቢ አሰባሰብ ሥርዓትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ  የቡርጂ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ገለጸ፡፡

መምሪያው የ2016 በጀት ዓመት ማጠቃለያ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ እና የ1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም መድረክ አካሂዷል፡፡

የቡርጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የኢኮኖሚ ክላስተር መመሪያ ኃላፊ አቶ ኮሬ አዶ በመድረኩ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በ2016 በጀት ዓመት የፋይናንስ ቴክኖሎጂን ከመጠቀም አንጻር የተሻለ ሥራ የተሠራ ሲሆን ከጥሬ ብር በተጨማሪ የኢ-ፋይናንስ አሠራር በስፋት ሥራ ላይ የዋለበት፣ በካፒታል በጀቱ በአግባቡ የተሠራበትና ከአጋር ድርጀቶች ጋር ጥሩ መስተጋብር የነበረበት ነው፡፡

የውስጥ ገቢ አሰባሰብ ሥርዓትን ማሻሻል፣ ድህነት ቀናሽ ሴክተሮችን ማጠናከር እና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ቁጥጥር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ኃላፊው አብራርተዋል።

በመድረኩ በጥንካሬ እና ውስንነት የተዳሰሱ ተግባራት የተገመገሙ ሲሆን ከግዥ እና ንብረት አስተዳደር አንጻር፣ የመንግስት ንብረት አያያዝ ችግር፣ የውስጥ ገቢ አሰባሰብ ስርዓት፣ በዞን ማዕከልም ሆነ በየቀበሌያት ያሉ የመንግስት ሀብቶች ብክነት በውስንነት ተነስተዋል።

አቶ ኮሬ እንዳመላከቱት ድህነት ቀናሽ ሴክተሮችን ማጠናከር፣ የመንግስት ሀብት አስተዳደርና ቁጥጥር ስርዐት ትኩረት መስጠት፣ የፋንናንስ እና የውስጥ አሠራር ስርአት ማሻሻል በ2017 በጀት ዓመት የዞኑ ፋይናንስ መምሪያ ዋና ዋና ግቦች ናቸው፡፡

የውስጥ ገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ለማሻሻል እና አላስፈላጊ ወጪዎችን ለመቀነስ እንዲሁም ያሉትን ውስን ሀብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለውጤታማነቱ የበኩሉን እንዲወጣም ተጠይቋል።

በጉባኤው አዲሱ የወረዳው የፋይናንስ አሠራር መመሪያ የቀረበ ሲሆን በያዛቸው ሀሳቦች ዙሪያ ውይይት ተካሂዶ ከዘርፉ መስሪያ ቤቶች ጋር የግብ ስምምነት ተፈርሟል።

ዘጋቢ: ወርቅአገኘሁ ወልደየስ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን