ከ5 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት የአበሽጌ ወረዳ የታች ገራባ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 11/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከ5 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት በዮሀንስ ሀይሌ

ኮንስትራክሽን ድርጅት የተገነባው የአበሽጌ ወረዳ የታች ገራባ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቋል።

በትምህርት ቤቶች ምቹ የመማሪያ አካባቢ ለመፍጠር ባለሀብቱ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታውቋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደገለፁት፥ ትምህርት ቤቶች ምቹ የመማሪያ አካባቢ በማድረግ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየተሠራ ይገኛል።

በእለቱ የተመረቀው ትምህርት ቤት ለተማሪዎች ምቹ የማድረግ ስራ ለውጤታመነቱ አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ የሚሠራው ስራ በመደገፍ የተማሪዎችን ቁጥርና ውጤት ለማሻሻል  የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

አክለውም የትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻልና የትምህርት ቁሳቁስ ለሟሟላት ሁሉም አሻራውን ሊያሳርፍ እንደሚገባ አስረድተዋል።

የአበሽጌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሡ ጁሀር በበኩላቸው፤ ትምህርት ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ እንደሀገር ብሎም እንደ ወረዳ ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ጥረቱ ከግብ ለማድረስ የሁሉም እገዛ እንደሚጠይቅ የተናገሩት አቶ ካሡ በታችኛው ገራባ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአቶ ዮሐንስ ሀይሌ ኮንስትራክሽን ድርጅት ድጋፍ የተገነቡት መማሪያ ክፍሎች ከ5 ሚሊየን ብር በላይ የወጣባቸው መሆኑን ገልፀው ተግባሩ ለሌሎች ባለሀብቶች አርዓያነት ያለው ነው ብለዋል።

የአበሽጌ ወረዳ ትምህርት ቤቶች ፅሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ እንግዳ ጥሩሀ እንደተናገሩት፤ በበጀት አመቱ ለትምህርት ንቅናቄ ተግባር ከ24 ሚሊየን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑ ጠቁመው፥ በአቶ ዮሐንስ ሀይሌ የተገነቡ መማሪያ ክፍሎችና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የትምህርት ቤቱ ደረጃ እንዲሁም የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል አስተዋፅዖው ከፍተኛ መሆኑን አመላክተዋል።

የመማሪያ ክፍሎች በመገንባትና የመማሪያ ቁሳቁስ በማቅረብ ለታችኛው ገራባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እገዛ ያደረጉት አቶ ዮሐንስ ሀይሌ በበኩላቸው፤ በስራ አጋጣሚ በትምህርት ቤቱ ሲያልፉ ተማሪዎች ምቹ ባልሆኑ ክፍሎች ሲማሩ በማየታቸው ይህን ድጋፍ እንዲያደርጉ መነሳሳታቸው ተናግረዋል።

ለትምህርት ቤቱ ባደረጉት የቁሳቁስ ድጋፍ በሕብረተሠቡ የተፈጠረው ደስታ እንዳስደስታቸው ገልፀው በቀጣይም ተደጋግፈን የድርሻችን እንወጣ ብለዋል አቶ ዮሐንስ።

የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና የተማሪ ወላጆች  የመማሪያ ክፍሎቹ በምቹ መማሪያ ክፍሎች በመቀየራቸው መደሠታቸውን ገልፀው ተማሪዎች ደረጃቸው በጠበቁ ክፍሎች እንንዲማሩ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ  ይገባልም ብለዋል።

 ዘጋቢ፡ አማረ መንገሻ – ወልቂጤ ጣቢያችን