የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር በመቀነስ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ገለፀ

በክልሉ በሀድያ እና ስልጤ ዞኖች በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች በላቭ ኢን አክሽን ኢትዮጵያ ግብረ ሰናይ ድርጅት በ3 ሚሊየን ብር ወጪ የተለያዩ የንግድ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል።

በመርሃ ግብሩ የተገኙት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታምራት ተስፋሁን እንደገለጹት በክልሉ የዜጎችን የስራ አጥነት ችግር ለመቀነስ ዘርፈብዙ ስራዎች እየተከነወኑ ነው።

በተያዘው በጀት ዓመትም ከ 3 መቶ 50 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን በቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፉት አራት ወራት ብቻ ከ46 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለፁት ኃላፊዉ፤ ከማምረቻና መሸጫ ቦታዎች ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ክፍቶችንም ለማስተካከል ይሰራል ብለዋል።

ላቭ ኢን አክሽን ኢትዮጵያ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት የወጣቶችን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ እየከናወነ ያለው ተግባር ዘርፉን የሚደግፍ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የላቭ ኢን አክሽን ኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ አክሊሉ ገ/ሚካኤል እንደገለጹት ድርጅቱ በትምህርት፣ በጤና እና የዜጎችን የኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ ላይ ለ23 ዓመታት እየሰራ ቆይቷል።

የወጣቶችን የስራ ባህላቸውን ከፍ ለማድረግና ኢኮኖሚያቸውን ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራት ላይ አየተሰራ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል።

ከጀርመን መንግስት የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሪ ጋር በመተባበር በክልሉ በሀድያ እና ስልጤ ዞኖች ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርግ የአምስት አመት የልማት ፕሮግራም በመቅረጽ ላለፉት ሁለት አመታት እየተሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል።

በሁለቱም ዞኖች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ከተሰማሩ 50 ማህበራት ውስጥ የተሻለ እንቅስቃሴ ላይ ለሚገኙ ለ26 ማህበራት የቴክኖሎጂ ክፍተታቸውን የሚሸፍኑ የ3 ሚሊዮን ብር የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።

ድጋፉ ቀጣይነት ያለው ስለመሆኑ በመጥቀስ በስራ ዕድሎች ሳይካተቱ የተገለሉና ከአገልግሎት ርቀው የሚገኙ የማህረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚነት ላይም በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም ነው አቶ አክሊሉ የተናገሩት።

ድጋፍ የተደረገላቸው ማህበራት በበኩላቸው የቁሳቁስ ድጋፉ በቴክኖሎጂ በታገዘ መልኩ ስራቸውን ለማንቀሳቀስ አጋዥ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀው፤ በስራቸው የበለጠ መነቃቃትን እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል።

ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ለስራው ማስጀመሪያ መነሻ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ከስራ አጥነት ችግር እንዲላቀቁ እንዳገዛቸውም ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮና በስልጤ ዞን ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብዱረህማን ወርቅቾ ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን