የአካባቢውን ማህበረሰብ መልካም ባህላዊ እሴቶች በማጎልበት ዘላቂ ሠላም ለማስፈን በየደረጃው በተቀናጀ አግባብ መስራት እንደሚያስፈልግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አስታወቀ
በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን በስፋት አርብቶ አደሮች የሚኖሩበት አካባቢ በመሆኑ ከሕብረተሰቡ አኗኗር ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የማህበረሰቡን ነባርና መልካም ባህላዊ እሴቶችን ማጎልበት ይገባል ያሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወላይቴ ቢቶ ናቸው።
ሀላፊዋ አያይዘዉም በአካባቢው በተለያዩ ምክንያቶች ለሚነሱ የፀጥታ ችግሮች መፍትሔ ለመሻት ከተንዛዛ አሰራሮች በመላቀቅ ፈጣን ምላሽ መስጠት ተጨማሪ ችግር እንዳይከሰት ይረዳል ብለዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ በበኩላቸው፤ ፀጥታን በማደፍረስ የገቢ ምንጭ የሚያደርጉ ጥቂት አመራሮችን በመለየትና ሠላምን ማስፈን የሁሉንም ብቁ ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።
ለፀጥታ ችግሮች መነሻ የሚሆኑ ምክንያቶችንና ወንጀለኞችን ከመቆጣጠር አኳያ ከጎሳ መሪዎችና ወጣቶች ጋር በመሆን በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አንፃራዊ ሠላም ማስፈን መቻሉን የዞኑ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ሀላፊ አቶ ጎላ ጉዳቦ እና በዞኑ የሳላማጎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኦሌሉ ቻርኒሌይ ገልጸዋል።
አመራሮቹ አክለውም ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት በአካባቢው ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ቀጣይነት ያለው ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ ዳኜ ጥላሁን – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጎልበት የጤና አደረጃጀቶችን ሚና ማሳደግ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ
ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመግባት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ትምህርታቸው ላይ ብቻ ሊያተኩሩ እንደሚገባ መልዕክት ተላለፈ
የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ