በማህበረሰቡ ውስጥ የተለመዱና የተዛቡ የስርዓተ ጾታ አመለካከቶችን ለመቅረፍ  ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 07/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማህበረሰቡ ውስጥ የተለመዱና የተዛቡ የስርዓተ ጾታ አመለካከቶችን ለመቅረፍ  ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ(CECOE) የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ በማስመልከት ከተለያዩ ተቋማት ለተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ሆሳዕና ከተማ  ስልጠና ሰጥቷል።

በሀገራችንም ሆነ በሌሎች የአለማችን ሀገራት የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎና የውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማሳደግ በመንግስትና በአጋር አካላት በኩል ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሲከናወኑ ይስተዋላል።

ይሁን እንጂ በተሰራው ልክ በሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በሚፈለገው ልክ ለውጥ እየታየ አይደለም፤ ይህን ችግር

ለመቅረፍ  ታዲያ ተከታታይ የአቅም ግንበታ ስልጠናዎች አስፈላጊ መሆናቸውን  በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅት ህብረት ለምርጫ  የፕሮግራም ኃላፊ አቶ ኢዩኤል ዘላለም ተናግረዋል።

ህብረቱ በተለይ ከምርጫ ጋር በተገናኙ የፖለቲካ ተሳትፎች ላይ ስራዎችን ይሰራል ያሉት ኃላፊው የዜጎችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የማህበረሰቡን አቅም የመገንባት ስራ ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

በስልጠናው የሲቪል ማህበራት፣ የሴት አደረጃጀት መሪዎች፣ የሚዲያ አካላትና ሌሎችም መሳተፋቸው ከስልጠናው ካገኙት  እውቀት በመነሳት በየመዋቅሮቻቸው የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ግንዛቤ እንደሚሰጡ ታሳቢ በማድረግ እንደሆነም አቶ ኢዩኤል አብራርተዋል።

የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ በማህበረሰቡ ውስጥ የተለመዱና የተዛቡ የስርዓተ ጾታ አመለካከቶችን መቅረፍ እንደሚገባና ለዚህም ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሚና እንዳለው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንትና አሰልጣኝ ወይዘሮ ታደለች ጭርቆ አስረድተዋል።

የሴቶች ጉዳይ የሁሉም ማህበረሰብ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ የሴቶች ጥቃትና ትንኮሳ ለመከላከል መረባረብና ተፈጽሞ ሲገኝም ባለቤትነት ስሜት መታገል እንደሚያስፈልግም ነው ያብራሩት አሰልጣኟ።

በፖለቲካ ውስጥ በሴቶች ላይ ለሚደርሱ ጥቃትና ለምርጫ ውስጥ በሴቶች ላይ ለሚደርስ ጥቃቶችንና ተግዳሮቶችን በመለየት ተሳቶፏቸውን ለመጨመር የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ  የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል፤ ሴቷ ራሷ በራሷ የመተማመን ብቃቷን ማሳደግ እንዳለባት አበክረው በመጠቆም።

ከስልጠና በኋላ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የስልጠና ተሳታፊዎች እንደተናገሩት የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በተመለከተ ለበርካታ ጊዜያት እና አጋጣሚዎች ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ለመስጠት በመቻሉ በማህበረሰቡ ውስጥ የቆየው ልማዳዊ የተዛባ አመለካከትና አስተሳሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ መጥቷል።

ነገር ግን በተለያዩ መንገዶች የሚገለጹ ልማዳዊ የሆኑ የተዛቡ አስተሳሰቦች በሚፈለገው ልክ አለመቀረፋቸው ለውጡ አዝጋሚ መሆኑን ማሳያ ናቸው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ለዚህም ማህበረሰቡ፣ ባለድርሻ አካላትና ሴቶች ራሳቸው ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ለማህበረሰቡ በቂ ግንዛቤ መስጠት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

በየጊዜው በሚሰጡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች  ላይ ከፊት ያሉ አመራሮችን   ብቻ ያከተተ ሳይሆን በተለይ የገጠሩን ክፍል ማህበረሰብ ያሳተፉ መሆን እንዳለበትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በስልጠናው የሲቪል ማህበራት፣ የሴትና የወጣት አደረጃጀት መሪዎች፣ የሚዲያ አካላትና ሌሎችም የተሳተፉ ሲሆን ለሁለት ተከታታይ ቀናት ተሰጥቷል።

ዘጋቢ፡ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን