የነዳጅ እና ቤንዚን ምርቶች ስርጭት ላይ የሚስተዋለውን ኢፍትሃዊነት ለመቅረፍ ጠንከር ያለ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ የወላይታ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መመሪያ አስታወቀ

የወላይታ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የነዳጅ ምርቶች እጥረትና በስርጭት በኩል የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ የምክክር መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የዞኑ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ዘውዱ ሳሙኤል፤ በህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከእነዚህም የነዳጅ ምርቶች እጥረትና ስርጭት ጋር ያለው ችግር በዋናነት የሚጠቀስ ነው ያሉት አቶ ዘውዱ፤ በዞኑ የሚገኙ የማደያ ባለቤቶች ጋር በመነጋገር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ነገር ግን ህገወጥ የነዳጅ ንግድን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የፍትህ አካላትን ጨምሮ የሁሉም ህብረተሰብ የጋራ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።

የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኃይሌ ስላስ በበኩላቸው፤ የነዳጅ እና ቤንዚን ስርጭት ላይ የሚስተዋለው ኢፍትሃዊነትን ለመቅረፍ ጠንከር ያለ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ከነዳጅ ስርጭት አኳያ የሚፈጸሙ ህገወጥ ተግባራት ተጠቃሚውን ህብረተሰብ ጨምሮ የንብረት ባለቤቶች ኢኮኖሚ ላይም ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ መሆኑን አቶ ስላስ ገልፀዋል።

በዘርፉ የሚስተዋለውን ኢፍትሃዊነትን ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ስሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት በዞኑ ሶዶ፣ ቦዲቲ እና አረካ ከተማን ጨምሮ ሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች ከአሠራር ውጪ የሚንቀሳቀሱ የማደያ ባለቤቶች መኖራቸው ተለይተው ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ሀላፊው ተናግረዋል።

ህገወጥ የነዳጅ ችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ግለሰቦች ጋር ማደያዎች በመመሳጠር የሚያደረጉትን ሴራ ለማክሸፍ በተጀመረው ጥረት ከተባባሪ አካላት ጭምር እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል።

በሁሉም ማደያዎች የግብይት ሥርዓቱ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ብቻ እንዲፈፀም በማድረግ ህገ ወጥ ደላላዎችን ከመሀል የማስወጣት ሥራ በተጠናከረ መልክ ለመስራት አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ በቀሌች ጌቾ እና አንዱአለመ ኡማ – ከዋካ ጣቢያችን