ሀዋሳ፡ ሕዳር 05/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) “ዞናዊ አንድነት ለጋራ ህልሞቻችን ለሁለንተናዊ ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የዞኑ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላትን ጨምሮ የዞኑ ተወላጅ የክልል አመራሮች የዞን ጠቅላላ አመራር እና የየወረዳ የፊት አመራሮች የምክክር መድረክ በደቡብ ኦሞ ዞን ዲመካ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
ለ2 ቀናት በሚቆየዉ የአመራር መድረክ በዞኑ ያሉ ፀጋዎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም የወደፊት የዞኑ ተስፋዎችና አቅሞች በሰነድ መልክ ለዉይይት ቀርቧል።
የዉይይት ሰነዱን ያቀረቡት የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ታደሰ ጋልጶቅ እንዳሉት ዞኑ በዓመት በትንሹ ከ1.8 ቢሊዬን ብር በላይ አመታዊ ገቢ የመሰብሰብ አቅም እያለዉ ነገር ግን ከዞናዊ አቅም ከ25በመቶ ያልበለጠ ገቢ መሰብሰቡ ቁጭት ሊፈጥር እንደሚገባ ተናግረዋል።
የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አነሳሽነት የተጀመረዉ አንድ መፅሀፍ ለአንድ ተማሪ ንቅናቄ 15ሚሊዬን ብር የሚጠጋ ሀብት ተሰብስቦ የመፅሀፊት ግዢ በመፈፀም ለትምህርት ቤቶች እየተሰራጨ መሆኑን አስታዉሰዋል።
በፀጥታ ሥራ የግጭት ነጋዴ የሆኑ አንዳንድ አካላት ከድርጊታቸዉ ታቅበዉ ለሠላም የድርሻቸዉን እንዲያበረክቱ የጠየቁ ሲሆን በቀጣይ ዞኑ የማስተካከያ እርምጃም እንደሚወስድ የመንግስት ዋና ተጠሪ ባቀረቡት ሰነድ አመላክተዋል።
በዞኑ ከ453,438ሄ/ር በላይ መሬት ሊለማ የሚችል ሀብት እንዳለ የገለፁት አቶ ታደሰ ቀደም ብለዉ ከገቡ አልሚዎች የናሳ፣ ፊርኤል እና ሉሲ የግል እርሻ ልማቶች የፍራፍሬ ምርቶቻቸዉን በቀጥታ ወደ ሱማሌ ላንድ በመጫን ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸዉን ተናግረዋል።
በእነዚህና ሌሎች ዝርዝር ተግባራት ዙሪያ ሰፋ ያለ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን በቀረቡ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ዉይይትና የመስክ ጉብኝት እንደሚኖር ከወጣዉ ፕሮግራም መረዳት ተችሏል።
በዉይይት መድረኩ የዞኑ ተወላጅ የሆኑ አመራሮች እየተሳተፉ ነዉ። በተመሳሳይ የዞኑ ተወላጅ ምሁራን መድረክም እንደሚኖር ከወጣዉ መርኸ ግብር መረዳት ተችሏል።
ዘጋቢ፡ ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
ህብረት ሥራ ማህበራት ለሀገር ብልፅግና መሪ ተዋናይ ናቸው ሲል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ገለፀ
በክራምት ወራት ሲከውኑት የነበረውን የበጎ ተግባር በበጋ ወራት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በስልጤ ዞን የሁልባረግ ወረዳ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ተናገሩ
ጥራት ያለውን ትምህርት ለዜጎች ለማድረስ እየተጉ ያሉትን ባለድርሻዎች ማበረታታት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን ፋይዳው የጎላ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ገለፀ