ሀዋሳ፡ ሕዳር 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለወባ ወረርሽኝ መራባት ምክንያት የሚሆኑ አካባቢዎችን የማጽዳትና ፍሳሾችን የማስወገድ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የቦንጋ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡
በከተማው “ረቡዕን ለወባ” በሚል የጽዳት ዘመቻ ለህንጻ ግንባታ ተቆፍሮ ለወባ ትንኝ መራቢያ የሆኑ ጉድጓዶችን ማዳፈን ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተከናውኗል።
በዕለቱ የተገኙት የካፋ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አጥናፉ ኃይሌ እንደተናሩት፤ ወባ እንደ ሀገር በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የጤና ቀዉስ በማድረስ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል።
ስርጭቱ በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ በመሆኑ ለዚህም ምክንያት የሚሆኑ የወባ መራቢያ ቦታዎችን እንዲሁም የግልና የአካባቢ ንጽህናን የመጠበቁ ስራን ባልተቆራረጠ መልኩ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቀጣይ በየደረጃው የሚገኙ አካላት “ረቡዕን ለወባ” በሚል የተጀመረውን ንቅናቄ አጠናክሮ በማስቀጠል ወረርሽኙን መከላከል ላይ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አስማማው አደመ በበኩላቸው፤ በከተማው “ረቡዕን ለወባ” በሚል የተጀመረው ዘመቻ መቀዛቀዙ ስርጭቱ እንዲባባስ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ጠቁመዋል።
በከተማው ለህንጻ ግንባታ የተቆፈሩ ጉድጓዶች ለወባ ወረርሽኝ መራባት መንስኤ በመሆናቸው ያቆረውን ውሃ የማዳፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን የቦንጋ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ አድማሱ አበራ ገልጸዋል።
በከተማው ከ2 ሺህ 4 መቶ ካሬ በላይ ለህንጻ ግንባታ የተቆፈሩ ጉድጓዶች መኖራቸውን ያነሱት ኃላፊው ቦታዎቹ ለወባ ወረርሽኝ መንስኤ በመሆናቸው ከተማ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የማዳፋት ስራ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በቀጣይም የኮረት ማምረቻና ሌሎች ለወባ ትንኝ መራባት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ቦታዎች የመድፈን፣ ዉሃውን የማፋሰስና የማጽዳት ስራ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል።
የዘመቻ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ማህበረሰቡ የወባ መራቢያ ቦታዎችን የማዳፈንና ማጽዳት ስራ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡ ሀብታሙ ኃይሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 120 የህክምና ዶክተሮችን አስመረቀ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ