ሀዋሳ፡ ሕዳር 03/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ጤፍ በማምረት ዉጤታማ መሆናቸዉን በጎፋ ዞን ቡልቂ ከተማ አስተዳደር በከተማ ግብርና ተደራጅተዉ የሚሰሩ ወጣቶች ተናግረዋል፡፡
በከተማው 147 ማህበራት በከተማ ግብርና፤ በአገልግሎት እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ተደራጅተዉ ስራ ላይ መሆናቸዉን በቡልቂ ከተማ አስተዳደር ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ጽ/ቤት አስታዉቋል፡፡
በጤፍ አጨዳ ላይ ካገኘናቸው የጽሬ ቀበሌ ፏፏቴ ሰብል ልማት ማህበር አባላት መካከል ወጣት ተገኝ ዱቃ፤ ወጣት እስራኤል ዱቃ እና አቶ ናትናኤል ዝናሬ በጋራ እንደተናገሩት፤ በ2016 ምርት ዘመን ጤፍን በማምረት ከአንድ ሄክታር ማሳ 10 ኩንታል ማግኘታቸዉን ተናግረዉ ምርቱን ከ120 ሺህ ብር በላይ በመሸጥ ሁለት ጥማድ በሬ መግዛታቸዉን ጠቁመዋል፡፡
በአንድ ለአምስት ተደራጅተዉ በሰሩት ስራ ዉጤታማ መሆናቸዉንና አሁን በጤፍ ምርት መሠብሰብ ላይ መሆናቸዉን ተናግረዉ ዘንድሮ ከአምናዉ የበለጠ ዉጤት እንደሚኖር ተስፋ እንዳላቸዉም አስረድተዋል፡፡
ወጣቶቹ በቀጣይ ሽንኩርትና ሌሎች ምርቶችን በስፋት ለማምረት ዕቅድ እንዳላቸዉ አንስተዉ የመሬት ጥበት ስላለ ተጨማሪ እንዲፈቀድም ጠይቀዋል፡፡
በአንድ ማዕከል ማምረቻና መሸጫ አስተባባሪ አቶ ሙላቱ ከበደ በበኩላቸው፤ በከተማዉ ለወጣቱ ስራ ዕድል ፈጠራ በርካታ ስራዎች የተሰሩ መሆናቸዉ ጠቁመዉ በከተማ ግብርና የተሻለ ዉጤት መመዘገብ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ወጣቶች በ2017 በጀት ዓመት በሶስት ዘርፎች 1ሺህ 350 የሚሆኑ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ልየታ መደረጉን ተናግረዉ፤ ከዚህ በፊት ከ5 ዓመት በላይ የቆዩ ማህበራት በጥቃቅንና አነስተኛ፤ በጥቃቅንና መካከለኛ እና የሚሸጋገሩ ማህበራትን ለይቶ መስራት እንደሚጠበቅ የመንግስት ረዳት ተጠሪና የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በኃይሉ ኤሊያስ ገልጸዋል፡፡
አክለዉም በዞኑ ኢኒሼቲቭ በከተማ አንድ ሄክታር እንዲያዘጋጁ በተደረገዉ መሰረት 1 ነጥብ 28 ሄክታር መሬት በኢንተርፕራይዝና ስራ ዕድል ፈጠራ መስራት ለሚፈልጉ ወጣቶች መዘጋጀቱን አብራርተዋል፡፡
ወጣቶች ላይ መስራት የነገ ኢትዮጵያን መስራት በመሆኑ ወጣቶች ለሚያነሷቸዉ የማምረቻ ቦታ፤ የገንዘብና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸዉን ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ: ኢያሱ አዲሱ – ከሳዉላ ጣቢያችን
More Stories
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በጌዴኦ ዞን ሁሉም ትምህርት ቤቶች በተለያዩ ኩነቶች ተከበረ
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ማጠናከር የክልሉ የመልማት አቅም ከፍ ያደርጋል – የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ