በኧሌ ዞን የኮላንጎ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ መደበኛ ጉባኤዉን አካሄደ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 02/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኧሌ ዞን የኮላንጎ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ መደበኛ ጉባኤዉን አካሂዷል፡፡

ምክር ቤቱ የ2017 አመት በጀትን ከ1 ሚሊየን 21 ሺህ ብር በላይ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮላንጎ ከተማ አስተዳዳር የምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ታኩና ጠለፌ እንደገለፁት፤ የከተማ አስተዳደሩ በመንግስት ይሁንታ የተደራጀ መሆኑን በመጠቆም ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት እንዲሁም መላዉ የኧሌ ህዝብ ህጎችና ደንቦች ብሎም ዕቅዶች ግብ እንዲመቱ የበኩላቸዉን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

የ2017 ዓ.ም በጀት ዕቅድ የአፈፃጸም ሪፖርት ያቀረቡት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ካንኩነሽ ኩሴ በበኩላቸው፤ የአገልግሎት አሰጣጥ በመንግስት አሰራር የግልፀኝነትና ተጠያቂነት አሰራር እንዲሰፍን በማድረግ፣ የተገልጋዩን እርካታና አመኔታ ማሳደግ፣ በህገ-መንግስቱ ድንጋጌ መሰረት መደበኛ ጉባኤዎችና ሪፎርሞችን እንደየአስፈላጊነቱ ማካሄድ እና የህዝቡ ይሁንታ የታከለበት ህግ ማዉጣት ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል።

በቀረበዉ ሪፖርት ላይ ከም/ቤቱ አባላት መካከል የድጋፍ ሃሳቦችና ጥያቄዎች ተነስተዉ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

በዚህም መሠረት የ2017 በጀት ዓመት በከተማ ም/ቤት ለተግባር ማስፈፀምያና ለደሞወዝ 508 ሺህ 872 ብር፣ ለሥራ ማስኬጃ 100 ሺህ ብር፣ ለአስገዳጅ ወጭዎች 400 ሺህ ብር፣ ለጥቅማጥቅም 12 ሺህ 600 ብር በአጠቃላይ 1 ሚሊየን 21 ሺህ 472 ብር ሆኖ ቀርቦ በምክር ቤቱ አባለት ሙሉ ድምጽ ጸድቋል።

የአሰፈፃሚ አካላት ሪፖርት ያቀረቡት የኮላንጎ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አልሶ አላሶ በሪፖርቱ እንደገለፁት፤ የከተማነት ዲዛይን የያዘ ፕላን መተግበር፣ በሚዲያ የታገዘ ለህዝብ ፍትሃዊነትና ተጠቃሚነት ይሰራል፡፡

ዘጋቢ፡ ተመስገን ንፍርቄ – ከጂንካ ጣቢያችን