ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ጎዳና ለማሻገር የማህበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው – የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር
ሀዋሳ፡ ሕዳር 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ጎዳና ለማሻገር የማህበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፍቀዱ ተናገሩ።
በስልጤ ዞን በአልቾ ዉሪሮ ወረዳ በማህበረሰብ አቀፍ ተሳትፎ የተገነባው የአብጀት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተመርቋል።
በምረቃ ኘሮግራሙ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የአልቾ ዉሪሮ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አማን ከድር፤ ባለፉት ዓመታት በወረዳው የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በርካታ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በገጠርና በከተማ የሚኖረውን ማህበረሰብ በመሳተፍ መገንባት መቻሉን ተናግረዋል።
በእውቀትና በስነ-ምግባር የበለፀገ ትውልድ ለማፍራት የትምህርት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው፤ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የአብጀት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እውን ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ በበኩላቸው፤ አለም ለደረሰበት የቴክኖሎጂ እድገት መሰረት ትምህርት በመሆኑ በዞኑ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት የማህበረሰብ ተሳትፎ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ዘርፍ የገጠመውን ስብራት ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ያለ ህብረተሰቡ ተሳትፎ ማረጋገጥ የማይቻል በመሆኑ ህብረተሰቡ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤቶች በመላክና በመከታተል ውጤታማ እንዲሆኑ ማገዝ ይጠበቅበታል ብለዋል።
የዞኑ ማህበረሰብ ለትምህርት በሰጠው ልዩ ትኩረት በለፉት ዓመታት ከ315.8 ሚሊዮን ብር በለይ ወጪ በማድረግ በርካታ የቅድመ መደበኛ፣ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መገንባት መቻሉን ተናግዋል።
በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፍቀዱ በበኩላቸው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ከፍ ለማድረግ በስነ-ምግባር የበለፀገ፣ ተወዳዳሪ ዜጋ ማፍራት ይገባል፡፡ ለዚህም የማህበረሰብ ተሳትፎ በማረጋገጥ የትምህርት ቤቶችን ስታንዳርድ በማሻሸል የትምህርት ጥራትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት “ጥራት የለው ትምህርት በማህበረሰብ ተሳትፎ” በሚል ንቅናቄ የበርካታ ትምህርት ቤቶችን ስታንዳርድ የማሻሻል፣ የመገንባትና የትምህርት ግብዓት በማሟላት የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ዛሬ ለተመረቀው የአብጀት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግብዓት ለሟሟላት የሚውል የ300 ሺህ ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
በማህበረሰብ ተሳትፎ የአዲስ አበባ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ሰሚር አወል፤ በከተማ የሚኖሩ የአካባቢውን ባለሀብቶችንና ነጋዴዎችን በማስተባበር በመንግስት ብቻ ሊሸፈኑ የማይችሉ የመሰረተ ልማት ስራዎችን በማገዝ የውሃ፣ የትምህርትና የጤና ጣቢያ ግንባታ ላይ አሻራቸውን መሳረፍ መቻላቸውን ተናግርዋል።
ያነጋገርናቸው ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ ከዚህ ቀደም ራቅ ወዳለ አጎራባች ቀበሌ ወደሚገኝ ትምህርት ቤት ያቀኑ በነበረበት ወቅት ያጋጥማቸው የነበረን እንግልት የሚያስቀር በመሆኑ ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተማሪ ወላጆችም ከዚህ ቀደም ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ፍለጋ ራቅ ወዳለ አካባቢ በሚጓዙበት ወቅት ያጋጥማቸው የነበረን ተግዳሮት የሚያቃልል በመሆኑ እጅጉን ደስተኞች ነን ብለዋል።
በዚህ የአብጀት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምረቃ ፕሮግራም ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፍቀዱ፣ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ፣ የአልቾ ውሪሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አማን ከድርን ጨምሮ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው አካላት፣ ተማሪዎች የተማሪ ወላጆች የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ ሙጂብ ጁሃር – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ