አዲሱ የቦንጋ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን የኡፋ እና የውሽውሽ ከተሞችን ያካተተ መሆኑን በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማት ዲን አቶ ደጉ በቀለ ገለጹ
ዲኑ ይህን የገለጹት የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የስትራክቸራል ፕላን ለማስጀመር ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው የውይይት መድረክ ነው፡፡
የከተሞች መዋቅራዊ ፕላን የአንድ ከተማን የረጅም ጊዜ አጠቃላይ ልማት አቅጣጫ የሚያሳይ ዋና ሰነድ ነው።
የመሬት አጠቃቀም፣ የመሠረተ ልማት አውታር፣ ማህበራዊ አገልግሎቶች፣ የከተማዋ መስፋፋት አቅጣጫ እና የአካባቢ ጥበቃን ያቀፈ ነው፡፡
የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተክለአብ ቡሎ (ዶ/ር) አስፈላጊ መረጃዎች ተሰብስበው ፕላኑ መሬት ላይ የሚወርድበት ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ ተናግረዋል፡፡
የከተማውን ማህበረሰብ የወከሉ አካላት በየደረጃው ውይይት እንደሚያደርጉም ነው የገለጹት፡፡
መዋቅራዊ ፕላኑ ውሽውሽና ኡፋ ከተሞችን እንዲሁም የገዳም ቀጠናን ያካተተ መሆኑንም ዶክተር ተክለአብ ገልጸዋል፡፡
ለተግባራዊነቱ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን በመወጣት ለወደፊት የተሻለች ከተማን መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡
ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በትኩረት መሠራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
የሚሰበሰቡ መረጃዎች ተገቢነት ላይ ሁሉም ተባባሪ ሊሆን እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
በከተማው አንድአንድ አከባቢዎች ላይ የሚስተዋሉ የናዳ ምልክቶችን ታሳቢ ያደረገ ፕላን ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማት ዲን አቶ ደጉ በቀለ፣ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት የሚቆየው ይህ መዋቅራዊ ፕላን መረጃን በማሰባሰብ 15 ሺህ ሄክታር የሚሸፍን ሆኖ ይወሰናል ብለዋል፡፡
ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር የሚዘጋጀው መዋቅራዊ ፕላን በጊምቦ ወረዳ የኡፋ እና የውሽውሽ ከተሞችን ያካለለ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ለኢንዱስትሪ፣ ለከተማ ልማት፣ ለመኖሪያ ቤትና ለኢንቨስትመንት ምቹ እንዲሆን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ፍቅሬ ገብሬ እና አቶ ጌታቸው ወልደሰንብት፣ ቦንጋ ከተማ በዙሪያው ያሉትን ውሽውሽና ኡፋ ከተሞችን በማካተት የፕላን ለውጥ ለማድረግ ሥራ መጀመሩ ለከተማው የቀጣይ ጊዜ ዕድገት አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ቦንጋ ከተማ ያላት ፕላን ከተማዋን መለወጥ ያለመቻሉን አንስተው፣ ማህበረሰቡ አዲሱ ፕላን ተግባራዊ እኅዲሆን የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
ከቦንጋ ከተማ ተነስቶ እስከ መካከለኛው ምስራቅ የሚደርስ የንግድ መነሻ ሆና ያገለገለች ጥንታዊ ከተማ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
የከተማነት ታሪኳ ረጂም ቢሆንም የእድሜዋን ያክል ማደግ ያለመቻሏ ቁጭት የሚፈጥርባቸው እንደሆነም ይገልፃሉ፡፡
ከሌሎች ከተሞች ዕኩል እንዳታድግ ደግሞ የመሠረተ ልማት ውስንነት፣ በተሻለ ፕላን ያለመመራት፣ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን ያለመቻል ዋና ዋና ተግዳሮቶች ናቸው ብለዋል፡፡
አዲሱ የ10 ዓመት መዋቅራዊ ፕላን የከተማዋን አጠቃላይ የዕድገት ደረጃ የሚወስን ይሆናል ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል፡፡
ታዲያ ይህ መዋቅራዊ የቦንጋ ከተማ ፕላን ገቢራዊ ይሆን ዘንድ የህብረተሰቡ፣ የተቋማት እና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፤- ዳንኤል መኩሪያ

More Stories
በሀሬ ተፋሰስበ በ27 ቀናት ወስጥ 35 ሄክታር መሬት ላይ እርከን ፣ አፈር እቀባና የተለያዩ ዕፅዋት ተከላ መከናወኑ ተገለፀ
የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን እንዲከበር ሲወሰን ዓላማው ብሔር ብሔረሰቦች ባህሎቻቸውን በመለዋወጥ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር ሃገራዊ መግባባትን እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው – የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር
20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያዊያን የምክክር ቀን መካሄድ ጀመረ