ህልማችን ልዕልና መር ነው – አቶ አደም ፋራህ

ህልማችን ልዕልና መር ነው – አቶ አደም ፋራህ

ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿን ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማሻገር ዓላማ አድርጎ የተነሳው የለውጥ ጉዟችን 6 አመታትን ተሻግሮ፣ ብልፅግና ፓርቲም ከተመሰረተ 5 አመታትን አስቆጥሮ በታላላቅ ስኬቶች እና ድሎች ታጅበን ዛሬ ላይ ደርሰናል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገልጸዋል።

ፈተናዎችን ተሻግረን፣ ጋሬጣዎችን ገፈን፣ ሰንኮፎችን ነቃቅለን ሊሳኩ የማይችል የሚመስሉ ድሎችን ማሳካት የቻልነው፣ ከባድ የሚመስሉ ወቅቶችን ለመሻገር አቅም ያገኘነው ህልማችን ልዕልና መር ስለሆነ ነው ሲሉም አቶ አደም ተናግረዋል።

አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በልዕልና መር ህልም እውን ማድረጊያ ጉዞ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ድሎችን አሳክተን ህዳሴ ግድብ ላይ ነፍስ ዘርተን፣ የሀገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎትን ከማሟላት አልፈን ኤክስፖርት አድርገን፣ በአጠቃላይ በፈተናዎች ያልተረታ ዘርፈ ብዙ አማራጮች ያሉበት ኢኮኖሚ ገንብተን ኢትዮጵያን በማሻገር ካይ እንገኛለን ብለዋል።

የተወረወሩብንን ቀስቶች አምክነን፣ ለውድቀታችን የተመከሩ ዶሴዎችን በብልሀት ቀደን፣ የተሰነዘሩብንን ጥቃቶች ቀልብሰን በአይደፈሬ ኢትዮጵያዊ ማንነት ህልውናዋ የተጠናከረ ሀምራዊት ኢትዮጵያን በብልፅግናዊ ብሩሻችን እየሳልናት እንገኛለን ሲሉም ገልጸዋል።

ኮይሻን ገንብተን፣ ጎርጎራን አስውበን፣ ጨበራ ጩርጩራን መስርተን፣ የወንጪን ውበት ገልጠን፣ አዲስ አበባን እንደ ስሟ በአበባነት ተምሳሌት ቀርፀን ያልተቋረጠው የልዕልና መር የህልም ጉዞ ዛሬም የበሰቃ ሀይቅን ውበት ሊያጎላ ብቅ ብሏል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

ከአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የ “ቤኑና መንደር” ግንባታ እነሆ ሌላኛው የልዕልና መር ጉዟችን ተጨማሪ ምስክርነት ሆኖ ዛሬ ለፍፃሜ መብቃቱ የተበሰረው በታላቅ ኩራት ነው ብለዋል።

ለእዚህም እንኳን ደስ ያላችሁ እንኳን ደስ ያለን ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።