ሙስሊሙ ማህበረሰብ አንድነቱን በማጠናከር ለአገር ሰላምና እድገት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሙሐመድ ኸሊል አሳሰቡ
ፕሬዝዳንቱ ይህንን የገለፁት የቀቤና ልዩ ወረዳ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በወልቂጤ ከተማ የምስረታ ጉባኤዉን ባካሄደበት ወቅት ነዉ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሙሐመድ ኸሊል በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ ሙስሊሙ ማህበረሰብ አንድነቱን በማጠናከር ለአገር ሰላምና እድገት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል።
የቀቤና ህዝብ በእምነቱ ጠንካራ እና የታላላቅ ኡለሞች መፍለቂያ ነዉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በልዩ ወረዳዉ ጠንካራ እስላማዊ ተቋም በመገንባት የቀደምት አባቶች ሀይማኖታዊ ስራዎችን ማስቀጥል ይገባል ብለዋል።
የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በክልሉ ከሚገኙ በሁሉም መዋቅሮች፣ ከፌደራል መጅሊስና ከሰላም ሚንስቴር ጋር በመቀናጀት በሰላምና ልማት ላይ እያከናወነ የሚገኘዉን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሀጂ ኢማሙ አሊያ በበኩላቸዉ፤ ልዩ ወረዳዉ የሚታወቅበትን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል ምክር ቤቱ በአፅንኦት ይሰራል ብለዋል።
የልዩ ወረዳዉ ሙስሊም ህብረተሰብ ይዞት የመጣዉን የመቻቻልና የአብሮነት ባህል ለማስቀጠል በሁሉም ቀበሌያት የተደራጀ የሀይማኖት ተቋም እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የልዩ ወረዳዉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ፀሀፊ ኡስታዝ ሙአዝ ሙደሲር፤ በልዩ ወረዳዉ የሙስሊሙን አንድነት እና አብሮነት ለማስቀጠል ባለፉት ወራት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።
ጠንካራ አደረጃጀቶችን በማዋቀር ህብረተሰቡ በተለይ ወጣቶች በእምነታቸዉ ጠንካራ ሆነዉ ለአካባቢያቸዉ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ምክር ቤቱ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የቀቤና ብሔረሰብ ከእስልምና ሀይማኖት ጋር በታሪክ የተገናኘ፣ በኢማም ሀሰን ዑንጃሞ መሪነት የራሱ እስላማዊ ህገ መንግስት እንደነበረዉ የገለፁት የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ፤ ተቋሙን ለማጠናከር የፌደራል እና የክልል መጅሊስ እንዲሁም መንግስት ያደረገዉ ጥረት የሚበረታታ መሆኑን አመላክተዋል።
በምስረታ ጉባኤዉ የክልሉ እስልምና ጉዳዮች እና የዑለማ ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚዎች፣ የልዩ ወረዳዉ ስራ አስፈፃሚዎች፣ የመስጂድ ኢማሞች፣ የኦገት እና የአገር ሽማግሌዎች፣ ዑለሞች፣ ኡስታዞችና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች የተገኙ ሲሆን የልዩ ወረዳዉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ አካላት ተመርጠዋል።
ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ከወልቂጤ ጣቢያችን
More Stories
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ