የንግዱ ማህበረሰብ የመንግስትን የልማት ጉድለት ለማሟላት የሚያደርገው ጥረት አበረታች መሆኑን የጋሞ ዞን ዋና አፈ ጉባኤ ገለጹ

የንግዱ ማህበረሰብ የመንግስትን የልማት ጉድለት ለማሟላት የሚያደርገው ጥረት አበረታች መሆኑን የጋሞ ዞን ዋና አፈ ጉባኤ ገለጹ

በዞኑ በገረሴ ከተማ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በንግድ ዘርፍ ማህበራት የተገነባው ህንጻ ተመርቋል።

በየአካባቢው የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች የህዝብ ተሳትፎ የሚሹ ናቸው።

በጋሞ ዞን በገረሴ ከተማ የሚገኘው የንግዱ ማህበረሰብ በከተማ አስተዳደሩ የሚስተዋለውን የቢሮ እጥረት ለመቅረፍ ከ1.7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የገነባውን ህንፃ ለከተማ አስተዳደሩ አስረክቧል።

የጋሞ ዞን ህዝብ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሪት አለሚቱ ዮሴፍ በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ የዞኑን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን የሚያግዝ የንግድ ማህበረሰብ ተፈጥሯል።

የንግዱ ማህበረሰብ በታማኝነት ከሚከፍለው ግብር ጎን ለጎን ለዞኑ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ የሚያደርገው ድጋፍ የመንግስትን ጉድለት የሚሞላ በመሆኑ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ጠይቀዋል።

የገረሴ ከተማ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት አቶ ወንዱ አበራ በበኩላቸው፤ የህዝቡ የመልማት ፍላጎት በመንግስት ጥረት ብቻ የሚሟላ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ የከተማ አስተዳደሩ የንግዱን ማህበረሰብ የሚያገለግልበት ደረጃውን የጠበቀ ህንፃ ገንብተን በማስረከባችን ደስተኞች ነን ያሉት አቶ አበራ፤ በሌሎች የልማት ስራዎችም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የገረሴ ከተማ ከንቲባ አቶ ኤርሚያስ እሸቴ፤ በለውጡ ዘመን የተደራጀው የከተማ አስተዳደር ሁሉ አቀፍ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በርካታ እቅዶች መኖራቸውን ተናግረው የንግዱ ማህበረሰብ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

ዘጋቢ፡ በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን